Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ኤድስ ቀን የፊታችን ቅዳሜ በፌደራል ደረጃ በዱከም ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም ኤድስ ቀን የፊታችን ቅዳሜ ህዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም በፌደራል ደረጃ በዱከም እንደሚከበር ተገልጿል።

በዓሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን፥ አሁን ላይ እየታየ ያለውን መዘናጋት በመስበር በየደረጃው የሚገኘው አመራርና አጠቃላይ ማህበረሰብ ቃሉን እንዲያድስ የሚደረግበት ነው ተብሏል።

የኤች አይ ቪ ስርጭት ምንም እንኳ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየቀነሰ ቢመጣም በክልል ከተሞች ግን ስርጭቱ እየጨመረ መምጣቱን ጥናቶች ይጠቁማሉ።

‘‘ለኤች አይ ቪ ይበልጥ ተጋላጭ ነን፣ እንመርመር እራሳችን እንወቅ በሚል መሪ ቃል’’ ህዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም በፌደራል ደረጃ በዱከም የሚከበረው ይህ በዓል በመላው ሀገሪቱ ታስቦ እንደሚውልም የፌደራል ኤች አይ ቬ /ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የኤች አይ ቪ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡን ግንዛቤና እውቀት ማሳደግና የባህሪ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራም ነው የተገለጸው።

ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኝባቸው ወገኖች የአስቸኳይ የድጋፍና ክብካቤ እንዲሁም ነጻ የጸረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት እንዲያገኙ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንደሚሰራም ተነግሯል።

በተጨማሪም ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም ሁሉን አቀፍ የኤች አይ ቪ/ኤድስ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ በፌደራል ደረጃ ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነው ተብሏል።

በዘቢብ ተክላይ

You might also like
Comments
Loading...