Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሃመድ አብዱላሂ ጎንደር ከተማ ገቡ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 30 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ጎንደር ከተማ ገቡ።

መሪዎቹ በአማራ ክልል ለሚያደርጉት ጉብኝት ዛሬ ጎንደር ከተማ ሲገቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፥ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አማካኝነትም ስለ ዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ገጽታ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

በጎንደር ቆይታቸው የተለያዩ ታሪካዊ ስፍራዎችን የሚጎበኙ ሲሆን፥ ከጉብኝታቸው በኋላም ወደ ባህር ዳር ያቀናሉ።

ባህር ዳር በሚኖራቸው ቆይታም የሶስትዮሽ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በውይይታቸው ቀጠናዊ ትብብርን ማሳደግና ማስፋትና የሃገራቱን ግንኙነት ማጠናከርና ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

ከዚህ ባለፈም ቀጠናዊ አብሮነትና ሰላም፣ ኢኮኖሚያዊ አንድነትና ውህደት እንዲሁም የጋራ ደህንነትና ሰላም የውይይታቸው አጀንዳ ይሆናል።

የመሪዎቹ ጉብኝት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሁለቱ መሪዎቹ አማራ ክልልን እንዲጎብኙ በይፋ መጋበዛቸውን ተከትሎ ነው።

ግብዣው በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ የሚገኘውን የለውጥ እንቅስቃሴና የኢኮኖሚ ትብብርን ለማመቻቸት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሚያካሂዱት እንቅስቃሴ አካል ነው ተብሏል።

መስከረም 2011 በአስመራ የተካሄደው የሶስትዮሽ ምክክር ተከታይ የሆነው ጉብኝት ውይይቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያለመ ሲሆን፥ በጎንደርና ባህር ዳር የሚገኙ የልማት እንቅስቃሴዎችን ጉብኝትም ያካትታል።

 

 

በዳዊት መስፍን

You might also like
Comments
Loading...