Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መሪዎች ባህር ዳር ገብተዋል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሃመድ አብዱላሂ ባህር ዳር ከተማ ገብተዋል።

መሪዎቹ ባህር ዳር ከተማ ሲደርሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አደርገውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ራሳቸው መኪና እያሽከረከሩም መሪዎቹን የባህር ዳርን ከተማ አዘዋውረው አስጎብኝተዋቸዋል።

መሪዎቹ ዛሬ ማለዳ ላይ በጎንደር ከተማ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ነው ባህር ዳር የገቡት።

ጠዋት ጎንደር ከተማ በነበራቸው ቆይታ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና በደምቢያ ወረዳ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።

ከዚህ ባለፈም ከሰዓት በኋላ የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ማቀነባበሪያ ፓርክም ጉብኝት አድርገዋል።

በባህር ዳር ከተማ በሚኖራቸው ቆይታም ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር የሶስትዮሽ ውይይት ያደርጋሉ።

በውይይታቸውም በአካባቢው የኢኮኖሚ ውህደት ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አተኩረው ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዳዊት መስፍን

You might also like
Comments
Loading...