Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ህብረት ማሻሻያ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ከ45 በላይ ሀገራት መሪዎች ይሳተፋሉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዋና ትኩረቱን የአፍሪካ ህብረት ማሻሻያ ላይ ባደረገው 11ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ ከ45 በላይ ሀገራት መሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ስብሰባው ነገ የሚጀምር ሲሆን፥ ብዙዎቹ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሰባሰቢያቸው አህጉራዊው ድርጅት የአፍሪካ ህብረት መሻሻል እንዳለበት ያምናሉ።

የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ግን ከማሰብም አልፈው ወደ ተግባር እንዲለወጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ተናግረዋል።

በ2016 ሩዋንዳ ኪጋሊ ላይ በተካሄደው የህብረቱ ስብሰባ የአፍሪካ ህብረት ማሻሻያ እንዲደረግበት ጥናት ተካሂዶ እንዲቀርብ ሀሳብ አቅርበዋል፥ ማሻሻያው በእርሳቸው አስተባባሪነት ላለፉት ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል።

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት የአህጉሪቷን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት አባል ሀገራቱን እያሰባሰበ፥ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እያስቀመጠ፥ የፋይናንስ አቅርቦትን እያፈላለገ አህጉራዊውን የዲፕሎማሲ ጉዞ በአንድ ድምፅ ሲያሰማ ቆይቷል።

አሁን ላይም በየአቅጣጫው በርካታ ፈተናዎች ቢደቀኑበትም የእኔ የሚለውን ጥረት እያደረገ ነው።

ህብረቱ ግዙፉን ፕሮጀክት አጀንዳ 2063ን ይፋ ካደረገም ሰነባብቷል።

ይህን በአህጉሪቷ ዘርፈ ብዙ ለውጥ የሚያመጣ አጀንዳ ይሳካ ዘንድ ግን እየተካሄደ ያለው ማሻሻያ ተግባራዊ የመሆኑ ጉዳይ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም።

የአፍሪካ ህብረት ላይ ተቋማዊ ማሻሻያ በማድረጉ እንቅስቃሴ ውስጥ አራት መሰረታዊ የትኩረት አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል።

በወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር እና የዚህ እንቅስቃሴ ፊታውራሪ መሪ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ አመራር መሰረት፥ ቅድሚያ ከተሰጣቸው የማሻሻያ ነጥቦች መካከል አንዱ የትኩረት አቅጣጫም ነው።

መሪዎቹ በበርካታ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በመወያየታቸው የአህጉሪቷን ዋና ዋና ችግሮች በአጭሩ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ ክፍተት ፈጥሯል በሚልም ትችቶች ይሰማሉ።

በዚህ የተነሳም የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ ውስጥ የተቀመጡ ምክረ ሀሳቦች እንዳሉም ይታወቃል።

ህብረቱ አህጉሪቷን የትኩረት አቅጫጫዎች የቀዳሚ ቀዳሚዎቹን ከመለየት አኳያ አንድ ዋና እና አንገብጋቢ ጉዳዮችን መርጦ መወየያየት፣ በተለይ የፖለቲካ የሰላም እና ፀጥታ እንዲሁም፥ የምጣኔ ሀብት ውህደት ላይ ማተኮር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ አንድ አፍሪካዊ ድምፅ ማሰማት ይጠቀሳሉ።

ከዚህም ሌላ በአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት በዋና ስራ አስፈጻሚዎች እና በሌሎች የህብረቱ የስራ ክፍሎች ያሉ የስልጣን መደቦችን በግልፅ ማስቀመጥ የሚሉ ተጨማሪ ጉዳዮችም አሉ።

የአፍሪካ ህብረት ድርጅታዊ አወቃቀር ዳግም የማደራጀት ሀሳብ በሁለተኛ ደረጃ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ነው።

የአሁኑ የህብረቱ አደረጃጀት ስምንት የኮሚሽን ዳይሬክቶሬቶች፣ 21 ዲፓርትመንት እና ኦፊሰሮች፣ 11 የህብረቱ ክፍሎች፣ 20 ከፍተኛ ኮሚቴዎች፣ 32 ልዩ የቴክኒክ ኤጄንሲዎች በስሩ ይገኙበታል።

በዚህ በተጀመረው የማማሻሻያ ሂደት ላይ የአፍሪካ ህብረትን ለዜጎቹ ሃላፊነት ይበልጥ እንዲሰራ ለማድረግ፥ የተቀመጡ ምክረ ሀሳቦች አሉ።

አወቃቀሩን ዳግም መከለሰ፣ ባለስልጣናቱ በሚመረጡበት ወቅት ሁለንተናዊ እውቅት ያላቸው መሆኑን ከግንዛቤ ማስገባት፣ የህብረቱን የቢሮክራሲ አሰራር ኦዲት ማድረግ፣ የወጣቶች እና የዜጎችን አስተዋፅኦ እና የግል ዘርፉን ውክልና ፍትሃዊ ለማድረግ ኮታ ማስቀመጥ፣ የአፍሪካ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጭዎች ቡድን ማቋቋም ያስፈልጋል።

የአፍሪካ ፓስፖርት አተገባበር ተግባረዊ ማድረግ፣ የህብረቱ እና ለአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት (ኔፓድ አባል ሃገራት) እንዲሁም የፓን አፍሪካ ፓርላማ እና የአፍሪካ ፍርድ ቤት አወቃቅርን ዳግም ማጤን እና ማስተካከል ይጠበቃል።

በሶስተኛ ደረጃ ህብረቱ በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፥ በዚህ የእስካሁኑ የማሻሻያ ሂደት ውስጥ ለመሪዎች የተቀመጠ ምክረ ሀሳብም መኖሩ ተገልጿል።

የቀድሞውን የጉባኤ አካሄዶችን በማሻሻል ህብረቱ የሚጥላቸው ማዕቀቦች ተግባራዊነታቸው እንዲጠናከሩ ማድረግ፣ የሰው ሃይል ምልመላ ሲካሄድ ብቃት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረግ እና በተለያየ ጊዜ የፍራንኮፖን እና አንግሎ ገጎን በሚል ክፍተት እንዳለ በትችት መልክ ሲደመጥ ይሰማል።

የህብረቱ ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበርን እና የሊቀ መንበሩን ዋና ኦፊሰር ሃላፊነት በግልፅ ማስቀመጥ የሚሉት ጉዳዮች ይገኙበታል።

ከዚህ ባለፈ ዋናው እና በተለይ በዚህ ዓመት ልዩ ትኩረት የተሰጠው የፋይናንስ ጉዳይ ነው።

ከትናንት በስቲያ አስቸኳዩ 20ኛው የስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ መክፈቻ ላይ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃማት እንደተናገሩት፥ አፍሪካ የምትተማመንበት እና የቆመችለት የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ጎዳና ክፉኛ እየተጎዳ ነው።

በዚህ የተነሳም አፍሪካውያን ይህ ሂደት የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የጋራ ድምፃቸውን ማሰማት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

ህብረቱን በፋይናንስ የማጠናከሩ ጉዳይም ፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን እናስቀድማለን ለሚሉ አባል ሀገራት ጊዜ የማይሰጠው የቤት ስራ ሆኗል።

ይሄኛው ዓመት ከመቼውም ጊዜ በላይ አፍሪካ የምታገኘው አለም አቀፍ ርዳታ የቀነሰበት ሲሆን፥ የአፍሪካ ህብረትን የፋይናንሰ እንቅስቃሴ እና ግኝት ስንመለከት ቁጥሮች ስጋት ውስጥ የሚከቱ ናቸው።

የህብረቱ በጀት ከ50 በመቶ በላይ ከእርዳታ የሚገኝ ሲሆን፥ የህብረቱ ፕሮግራሞች 97 በመቶ የእርዳታ እጆችን የሚጠብቁ ናቸው።

እነዚህ ጉዳዮች የህብረቱን መሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ ጉባኤ እንዲጠሩ አስገድደዋል።

የኢትዮ ኤርትራ አዲስ የሰላም ስምምነት በየጊዜው ለህብረቱ ስብሰባ ዋና አጀንዳ የሚሆነውን ቀጠናዊ ትርምስ በተስፋ መንገድ እየመራው የሚገኝ ሲሆን፥ ከላይ ከተጠቀሱት ምልክቶች ባለፈ የተስፋ ንፋስም እየነፈሰ ነው።

በስላባት ማናዬ

You might also like
Comments
Loading...