Fana: At a Speed of Life!

የራሳቸውን ህንጻ ዘግተው የሚከራዩ ተቋማት ይዞታቸው ሊነጠቅ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2011 (ኤፍ.ቢሲ) የራሳቸውን ህንጻ ዘግተው የሚከራዩ ተቋማት ይዞታቸው እንደሚነጠቅ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የገንዘብ ሚኒስቴር በዓመት እስከ አንድ ቢሊየን ብር ለህንጻ ኪራይ የሚያወጣ ሲሆን፥ ተቋማት ወጪ ቁጠባን መሰረት ያደረገ ስራ መስራት እንደሚገባቸው አሳስቧል።

የመስሪያ ቦታ እያላቸው ውጭ ከተከራዩ ተቋማት መካከል የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አንዱ ሲሆን፥ በቅርቡ ነባሩን የተቋሙን ህንጻ በማደስ ወደ ራሱ ህንጻ መመለሱ ተነግሯል፡፡

ልማት ድርጅቱ በአዲስ አበባ ከ14 በላይ ይዞታዎች ቢኖሩትም ከዓመታት በፊት በፒያሳ የሚገኘውን ህንጻ በመተው በዓመት በ14 ሚሊየን ብር ወጪ ሌላ ህንጻ ተከራይቶ እንደነበር ተገልጿል፡፡

በዚሁ ምክንት ድርጅቱ የተበታተነ መስሪያ ቤት መሆኑና የኪራዩ መጠን በየዓመቱ እየጨመረ መቀጠሉ ትርፋማነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደፈጠረ ተነስቷል፡፡

የድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ እርምጃው በሁሉም ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

ቀድሞ የነበሩት አመራሮች መከራየቱን የፈለጉበት ምክንያት በውል የተቀመጠ ነገር ባይኖርም ህጋዊ የጨረታ ሂደትን ተከትለው ህንጻውን መከራየታቸው ተገልጿል፡፡

በስራው ሂደት ደስተኛ የሆነው ሰራተኛም በራሱ ጉልበት ህንጻውን አድሶ ያለምንም ወጪ ወደ ራሱ መስሪያ ቤት መመለሱም ተነስቷል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ለፌደራል መስሪያ ቤቶቿ በዓመት እስከ አንድ ቢለየን ብር ለኪራይ እንደምታወጣ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት 12 ተቋማት ግንባታ ተከናውኖላቸው በራሳቸው ህንጻ እንዲገቡ ያደረገ ሲሆን 20 ለሚጠጉ ተቋማት ደግሞ ተጨማሪ ግንባታ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ሆኖም በአሁኑ ወቅት ህንጻ ኖሯቸው የሚከራዩ ተቋማት በራሳቸው የሚከራዩበትን ሂደት ዝግ መደረጉን የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀጂ ኢብሳ ገልጸዋል፡፡

ህንጻ ኖሯቸው ሌላ ቦታ የተከራዩ ተቋማትም እንዲመለሱ የተነገራቸው ሲሆን ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ሚኒስቴሩ ተረክቦ ግንባታ ይፈጽምበታል ብለዋል፡፡

 

በኃይለኢየሱስ ስዩም

You might also like
Comments
Loading...