Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ የ2025 ግቡን በማሳካቱ የ2030 ዕቅድን አዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2025 ግቡን ቀድሞ በማሳካቱ የ2030 እቅድ ማዘጋጀቱን አስተስወቀ።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ ገብረማርያም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ባለፈው ዓመት 11 ሚልየን ተጓዦችን ማስተናገዱን ገልጸው 9 ነጥብ 5 ሚሊየኑ ዓለም አቀፍ ተጓዦች መሆናቸውን አንስተዋል።

ይህንን ከግምት በማስገባት ሀገሪቱን የማስተዋወቅ ስራ ለመስራት የበኩሉን ለመስራት ማቀዱን ገልጿል።

አየር መንገዱ በመግለጫው የቱሪዝም እና ሆቴል ዘርፉንም ለማነቃቃት የሆቴል ግንባታ እያደረገ መሆኑን አንስቶ፥ ለቱሪስቶቹም 373 ክፍል ያለው ባለ 5 ኮከብ ሆቴል እየገነባ መሆኑ ገልጿል።

ለአፍሪካ ሀገራት የቪዛ ማዕከል በመሆንም ቪዛ ለመውሰድ ያለውን ሂደት ለማገዝ ማሰቡንም ጠቅሷል።

በመጨረሻም በአፍሪካ ቀዳሚ ዓየር መንገድ ለመሆን መብቃቱን ያስታወቁት ዋና ስራ አስፈፃሚው አየር መንገዱ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶችም ድጋፍ እያደረገ መሆኑን እና የማስተዳደርና የባለቤትነት ድርሻውን እያሰፋ መምጣቱን አንስተዋል።

ከሰራተኛ፣ ከመልካም አስተዳደር እና የአውሮፕላን ግዥን በተመለከተ ከመገናኛ ብዙኀን ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

በምላሻቸውም የሰራተኞች ቅሬታን በተመለከተ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተቋሙ ከሚከተለው ጥብቅ የዲስፕሊን እና የስራ አፈፃፀም ጋር በተያያዘ መሆናቸውን እና በየደረጃው የሚነሱ ቅሬታዎች የሚታዩበት ስርአት እንዳለ ያስታወሱት አቶ ተወልደ፥ በጥብቅ ቁጥጥሩ እና አፈፃፀም መሻገር የተሳናቸው ተቋሙን ከለቀቁ በኋላ ሊስሉ የሚሞክሩት ፓለቲካዊ መልክ ትክክል እንዳልሆነ አስረድተዋል።

የፕሮቶኮል፣ የስራ ሰዓትን አለማክበር፣ የዲሲፕሊን ግድፈቶች፣ እንዲሁም ፓይለቶችን ጨምሮ በየጊዜው የሚፈተሹ የአፈፃፀፀም ውጤቶች ማነስ ለሰራተኞቹ ቅሬታ እና ቁጣ ምክንያት መሆናቸውን የተቋሙን አለም አቀፋዊነት እና ከሌሎች የመንግስት ተቋማት ጋር አለመመሳሰል አጣቅሰው ተናግረዋል።

በየጊዜው የሚነሱ የፓለቲካ መልክ የተሰጣቸው ቅሬታዎችም እነዚህን መስፈርቶች እና አለምአቀፉ ተቋም የሚጠይቀውን ባለማሟላት የሚወሰድባቸውን ከደረጃ ዝቅ የማድረግ እርምጃ ካለመቀበል የመጣ ነው ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው።

ፓለቲካው በተቀያየረ ቁጥርም በውጤታማነቱ መቀጠሉ ፓለቲካው ወደ አየር መንገዱ እንዳይገባ በሚደረገው ጥረት መሆኑን አንስተዋል።

አያይዘውም ማንም በብሄሩ ወይንም በሀይማኖቱ የተለየ ችግር የደረሰበት አለመኖሩን ነው የተናገሩት።

አለም ዓቀፉ የአቬዬሽን ደህንነት በከባድ ችግርነት ያሰቀመጠውን ስህተት ፈፅመዋል ያላቸውን ፓይለቶች ተቋሙ ላይ ያደረሱትን ጉዳት ከግምት በማስገባት እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰው፥ ሰራተኞቹ ባልተገባ መንገድ ስም ለማጥፋት ተንቀሳቅሰዋል ብለዋል።

የተቋሙ አመራሮች አባይ የሊዝ ካምፓኒ በመፍጠር አውሮፕላን በግላቸው እያከራዩ ነው በሚል እየተናፈሰ ያለው ወሬ አለም አቀፍ አሰራርን ካለመገንዘብ የመነጨ መሆኑን በማንሳት፥ አውሮፕላን ሲገዛ ለማያስያዣነት የሚፈጠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከተገዙ አውሮፕላኖች መቆም ጋር በተያያዘም በሞተሮቹ አዲስነት አልፎ አልፎ የሚፈጠር መሆኑን አንስተው፥ በዘርፉ የተለመደ ችግር መሆኑን እና ግዢያቸው ግን ተቋሙን በሚያዋጣ መልኩ የተከናወነ መሆኑንነው የገለፁት።

ሜቴክ ገዝቷቸዋል ከተባሉት አውሮፕላኖች ጋር በተያያዘም አየር መንገዱ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ እና የሜቴክ አውሮፕላኖችም በግቢው ውስጥ እንደሌሉ አረጋግጠዋል።

 

በሃብታሙ ተክሌ

You might also like
Comments
Loading...