Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ከወባ በሽታ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል- ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ከወባ በሽታ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን የጤና ጥበቃ ሚኒቴር አስታውቋል።

ባለፉት 5ዓመታት የወባ ትንኝ መራባትን የመቆጣጠር ስራ፣ የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት፣ የአጎበር ስርጭት፣ የህክምና አገልግሎት አቅርቦትን የማጠናከር ስራዎች በመከናወናቸው በወባ የሚጠቁና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት የወባ መከላከል ኬዝቲም አስተባባሪ አቶ መብራሃቶም ኃይለ ገልጸዋል።

ላለፉት 15 ዓመታት የወባ ወረርሽኝ ስለመከሰቱ ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሪፖርት አለመደረጉን የተናገሩት አቶ መብራሃቶም በየጊዜው የተመዘገበውን የወባ ወረርሽኝ መቀነስ አዝማሚያ የተረዳው የዓለም ጤና ደርጅትም ለኢትዮጵያ ዕውቅናና ሽልማት ማበርከቱን አስታውሰዋል።

ሰሞኑን የአለም ጤና ድርጅት ባሰራጨው ሪፖርት መሰረትም በኢትዮጵያ እኤአ ከ2016 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት 40 በመቶ የወባ ስርጭትን ለመቀነስ የተያዘውን ዕቅድ 2018 ላይ ሆና 35 በመቶ ላይ መድረሷን ጠቅሶ አስፍሯልም ብለዋል።

ከስድስትና ሰባት ዓመታት በፊት በዓመት እስከ ስምንት ሚሊየን ሰዎች በወባ እንደሚያዙ ሪፖርት ይደረግ ነበር ያሉት አስተባባሪው ባሳለፍነው ዓመት ሪፖርት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ያህል ብቻ ሰዎች በወባ መያዛቸው ረፖርት መቅረቡ ለውጥ እንዳለ ያሳያል ብለዋል።

በአፍሪካ የወባ ወረርሽኝ እየጨመረ ስለመምጣቱ ሪፖርት እንደደረሰው የአለም ጤና ድርጅት የገለፀ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ፣ ፓኪስታን፣ ሩዋንዳና ህንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወባ ወረርሽኝ የቀነሰባቸው ሀገሮች ሆነው መመዝገባቸውን ነው የሚናገሩት።

በአገር አቀፍ ደረጃ እኤአ በ2030 ወባን ጨርሶ ለማጥፋት የተያዘውን ፕሮግራም ለመተግበር የሚያስችሉ ቅድመ ስራዎችን ለመገምገም የሚያስችል ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ መሆኑን የጤና ጥበቃ መረጃ ያስረዳል።

You might also like
Comments
Loading...