Fana: At a Speed of Life!

በህይወት ማጥፋትና አካል ማጉደል በተጠረጠረው ቴዎድሮስ አዲሱ ላይ የ12 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሶማሌ ክልል ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረግ የበርካታ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋ፣ ንብረት እንዲወድምና በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ፣ በመምራትና በመቀስቀስ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠረው ቴዎድሮስ አዲሱ / ቴዲ ማንጁስ/ ላይ ፍርድ ቤቱ የ12 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

መርማሪ ፖሊስ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት አስቀድሞ በሰጠው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ግለሰቡ የፈፀማቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርቧል።

ተጠርጣሪው ሲጠቀምባቸው የነበሩ ሞባይልና ላፕቶፖችን ለቴክኒክ ምርመራ መላኩን፣ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ፣ ቀብሪ ዳህርና ደጋሃቡር ከሚገኙ ምስክሮች ቃል መቀበሉን፣ ተጠርጣሪው ቀድሞ በክልሉ ከነበሩ ባልስልጣናት ጋር በነበራቸው ጥብቅ ግንኙነት ሁከትና ብጥብጡ ለማከናውን ተብሎ ወጪ የተደረገውን ገንዘብና ማስረጃ ሰነዶች ማስመጣቱን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

በቀጣይም በሶማሌ ክልል ጉዳት የደረሰባቸውን 37 ሰዎች ጉዳት የሚገልፅ ሰነድ ማምጣት፣ የምስክሮችን ቃል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ መቀበል፣ የጦር መሳሪያ፣ የገንዝብ መጠንና በክልሉ ጅግጅጋ ከተማ የንግድ ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማስተርጎም በመዘርዝር የ28 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪው በጠበቃቸው በኩል በግልፅ ተጠርጣሪውን በተመለከተ የተሰራው ስራ አለመቀመጡን፣ ሰነዶችን ለማስተርጎም ተጠርጣሪው መብታቸው ተገድቦ በእስር መቆየት የሌለባቸውና ሌሎች የመከራከሪያ ሀሳብ አቅርቧል።

በተለይም በሶማሌ ክልል የሚገኘው ማተሚያ ቤታቸው የተዘጋ በመሆኑ የባንክና ከታዘዙት ስራ ጋር በተገናኝ 17 ሚሊየን ብር ብድር ያለባቸው የ3 ልጆች አባትና በቂ አድራሻ ያላቸው በመሆኑ በዋስትና እንዲለቀቁ ጠበቃው ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ያከናወናቸውን ስራዎች በመመርመር በርካታዎቹ ስራዎች የተከናውኑ በመሆኑ የምስክሮችን ቃል ብቻ ለመቀበል ለመርማሪ ፖሊስ የ12 ቀን ጊዜ በመፍቀድ ለታህሳስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በበላይ ተስፋዬ

You might also like
Comments
Loading...