Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ላይ ያደረጉት ንግግር

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ላይ ያደረጉት ንግግር።

ክብርት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ፤
ክብርት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ፤
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት፤
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች ፤

ክቡራትና ክቡራን ፤
አሮጌውን ዓመት ሸኝተን ወደ አዲሱ ዓመት በተሸጋገርንበት በዚህ በመስከረም ወር የመጨረሻ ሰኞ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት በሚደነግገው መሠረት የሁለቱ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን መጀመርን በይፋ ለማብሰር በሚከናወነው የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝቼ ንግግር እንዳደርግ በመቻሌ ልባዊ ደስታ የተሰማኝ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ በንግግሬም እንደሀገር ያለፈውን ዓመት አፈጻፀም በአጭሩ፤ በዋነኝነት ግን የ2011 በጀት ዓመት የመንግስት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫ አመላካች ነጥቦችን አነሳለሁ፡፡

ያለፈው ዓመት በዓይነቱ የተለየ እንደነበረና አገራችንም በከፍተኛ የለውጥ መዘወር ውስጥ ገብታ የነበረችበት እንደነበረ ሁላችንም የምናስታውሰው ነው፡፡ ምንም እንኳ ታላላቅ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕቅድ አልመን ለማሳካት ብንነሳም በአገራችን በነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ባቀደነው ልክ መፈጸም ሳንችል ቀርተናል፡፡

ለበርካታ ዓመታት – መንግስታችን የህዝቡን መሰረታዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ የተከተለው ዘገምተኛ አካሄድ – አገሪቱን በአሳሳቢ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትገኝ አድርጓት ነበር፡፡

ብዝሃነትን የምታስተናግድ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለማነፅ በተጋንበት መጠን ሁሉ ኢ-ፍትሃዊና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አሰራሮች የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ፈተና ውስጥ አስገብተውታል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፤ እንዲሁም ቁልፍ የዲሞክራሲ አስተዳደር ተቋማትን በማጠናከርና የአሰራር ነፃነታቸውን ከማስጠበቅ አንፃር የተከተልነው ያልተሟላ አካሄድም ህዝባችን አማራጭ የትግል መድረኮች እንዳይኖሩት፤ የህዝብ አይንና ጆሮ የሆኑ ተቋማትም ጎልተው እንዳይወጡ፤ ትርጉም ያለው የሲቪል ማህብረሰብ እንቅስቃሴም እንዳይኖር ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡

በአጠቃላይ ከወሳኝ ባለድርሻ አካላት ጋር ሀገራዊ መግባባትን ባልፈጠረ የፖለቲካ ምህዳር ብቻችንን ስንዳክር ቆይተናል፡፡ ዜጎቻቻንም በፍትህና የአስተዳደር በደሎች ሲሰቃዩና የዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶቻችው ሲጣበቡ እና ሲጣሱ እያየን – በዕለት ተዕለትና የአጭር ጊዜ ዕይታዎች ተውጠን – ችግሮቹን ከምንጮቻቸው የሚያደርቁ ዘመን ተሻጋሪ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎችን ሳንወስድ ለረጅም ጊዜ ቆይተን ነበር፡፡

ከዚህ መነሻ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ዝርዝር ግምገማ በማካሄድ ተገቢውን የአመራር ለውጥ ጭምር በማድረግ ችግሩን በአዲስ የለውጥ እርምጃ መፍታት በመጀመሩ አገራችን ላይ ዳግም የተስፋ ጎህ እንዲቀድ ሆኗል፡፡

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት፥ከእነዚህ ጥልቅ ክፍተቶቻችንና ችግሮቻችን አንፃር – የሀገራችንን ቀጣይ ህልውና ለማረጋገጥና የህዝባችንን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ – በመንግስት አስተዳደር ስርአታችን ላይ መሰረታዊ ለውጦችን በአፋጣኝ ተግባራዊ ማድረግ – ለእኛ እንደ ምርጫ የሚቀርብ ሳይሆን ወቅቱ ፍፁም ግድ የሚለው አንገብጋቢ ጉዳይ ነበር፡፡ ከዚህ በመነሳት ነባራዊ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ሁኔታዎቻችንን በፅሞና በመመርመር ወደ ስልጣን የመጣው አዲሱ አመራር ለህዝባችን ጥያቄና ፍላጎት በመገዛትም በሁሉም ዘርፍ አዲስ ታሪክ ለመፃፍ የምንንደረደርበትን ወሳኝ የፖለቲካ ምዕራፍ ጀምሯል፡፡

መንግስታችን በተከተለው የፍቅር፣ የይቅርታና መደመርን መሠረት ያደረጉ ተጨባጭ እርምጃዎች ሀገራችን ተጋርጦባት ከነበረው ቀውስ የታደገ ብቻ ሳይሆን ዜጎችም በሀገራቸው ዕጣ ፈንታ የሩቅ ተመልካች ሳይሆኑ ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ምቹ መደላደል ፈጥሯል፡፡ በዚህ ረገድ በመንግስት ከተወሰዱት አበረታችና ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች መካከል ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ፡-

• የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ብሎም ሀገራዊ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት እንዲቻል በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ከእስር በይቅርታ እንዲፈቱ ተደርጓል፤

• በፖለቲካል ዘርፍ ሰለማዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ውይይት ለማጠናከር መሰረታዊ የለውጥ እርምጃ በመውሰድ የነፍጥ ትግል ስልትን መርጠው በስደት ላይ ከቆዩትም ሆኑ በሀገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ውጤታማ ድርድሮች ተካሂደዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በውጭ አገር የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ቤት ገብተው በብሄራዊ የፖለቲካ አውዱ ያለምንም ስጋት መንቀሳቀስ እንዲችሉም ተደርጓል፤ ይህንንም ለማስቻል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅድሚያ ሰጥቶ የምህረት አዋጁን ማጸድቁ ለዚህ ጉልህ አስተዋጾ አበርክቷል፡፡

• ኢትዮጵያውያን በግልም ይሁን በቡድን ተሰባስበው፣ እንደ ፓርቲ፣ እንደ ንቅናቄ፣ እንደ ሲቪል ማህበረሰብ፣ ወዘተ ያለ ፍራቻ እና በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችሉበትን ምህዳር በመፍጠር ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ተንታኞች፣ ማህበራዊ አክቲቪስቶች፣ ጦማሪያን፣ እና ሌሎችም ሀሳብ አመንጪዎች፣ አገራቸው የእነርሱም ጭምር መሆኗን ተረድተው ፣ እኔም ያገባኛል ብለው በፍቅርና በእርቅ፣ በመደመር እና በአንድነት ለአንድ ሀገር በሠላም የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

• መንግስት ከአገር ውጭ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ማህበረሰብ በአገራቸው የኢኮኖሚ ልማት፤ የዲሞክራሲ ግንባታ እና አገራዊ ሰላም በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ የተደረገ ሲሆን፤ በተለይም በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ሰፊ ውይይት ከማድረጉም በላይ የጥላቻን ግድግዳ በማፍረስ ለፍቅርና አንድነት ድልድይ ትልቅ መሰረት ጥሎ አልፏል፤

• በተመሳሳይም ከሁለት አስርተ አመታት በላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አመራሮች ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ልዩነት እና በዚህም ቤተክርስትያኗ ለሁለት ተከፍላ የቆየች የነበረ ሲሆን በዚህ ታሪካዊ የዕርቅ ሂደት አንድ ወሳኝ ምዕራፍ በመሆን ሁለቱም ወገኖች ወደ አንድነት እንዲመጡ ተደርጓል፤

• በውጭ ጉዳይ ግንኙነታችን የኢትዮጵያና የኤርትራን ጥቅሞች ማዕከል ያደረገ አዲስና ሁሉን-አቀፍ ግንኙነት ለመመስረት የሚያስችል ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህን ተከትሎም ተስፋ ሰጪ የሆነ የግንኙነት ምዕራፍ ከፍተናል፡፡ ߵየአፍሪካውያን ችግር በአፍሪካውያን መፍታትߴ በሚለው አህጉራዊ መርህ በመመራት በሰራናቸው ስራዎች – ዛሬ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካካል የነበረው የጥላቻና የመጠፋፋት ፖለቲካ

– ዘላቂ ሰላምን፤ የጋራ ተጠቃሚነትና ኢኮኖያሚያዊ ውህደትን ማዕከል ባደረገ አዲስ የፖለቲካ ግንኙነት ማዕቀፍ እንዲተካ ሆኗል፡፡ ይህ አካሄዳችን ከሁለቱ አገራት ባሻገር – የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም፤ ዘላቂ እድገትና ትብብርን በማጠናከር – የቀጣናው ዋና መገለጫ ሆኖ የኖረውን የድህነት፤ የጦርነትና የአለመረጋጋት አዙሪትን የቀየረ ታሪክ ለማድረግ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

• በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል ከሁለት ዓመት በላይ ተቋርጦ የቆየው የሰላም ስምምነት በኢጋድ ሊቀመንበርነችን ዳግም ህይወት እንዲዘራ መደረጉ፣

• ኢትዩጵያ ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳን፣ ከዩጋንዳ፣ ከግብጽ ጋር ያላትን መተማመንን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ያጠናከረችበት፣ ከዛም አልፎ በቀጣናው ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት ከሁለት የመካከለኛ ምስራቅ ሀገሮች ማለትም ከተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የተፈጠረው የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት፣ ከፍ ሲልም የኢንቨስትመንት ዕድል እንዲመቻች መደረጉ፣

• ኤርትራ ከሶማሊያ እና ኤርትራ ጅቡቲ ጋር የነበራቸውን ቅራኔ በማለዘብ ሂደት ኢትዮጵያ እንደ ኢጋድ መሪ ጭምር ያበረከተችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ፣

• በዚህ አጋጣሚ – ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ለተደረሰው ሰላም እንዲሁም እየተጠናከረ ለመጣው የአየርም ሆነ የየብስ የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት በአጠቃላይ በዚህ ዙሪያ ለተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶች – ከጅምሩ ጀምሮ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉትና ያለማሳለስ ከልብ በመነጨ ስሜት ለደከሙት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዲሁም ለሀገረ-ኤርትራ ፕሬዚደንት ለክቡር አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ልባዊ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ እነዚህ የለውጥ እርምጃዎች ሀገርን ከቀውስ ወደሰላም የመለሱ የድልና ስኬት ትርክቶች ብቻ ሳይሆኑ በታሪክ የቀዳሚነትን ድርሻ የሚይዙ ክንውኖችም ናቸው፡፡

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት፥

መንግስት ሰላምና የተረጋጋ ሀገር መፍጠርና በዚሁ ሁኔታ ማስቀጠል የሚቻለው የተሟላ የዴሞክራሲ ስርአት ሲፈጠር ነው ብሎ ያምናል። የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ስራ ፅኑ ተቋማዊ መሰረት ከሌለው ረጅም መንገድ ሊጓዝ እንደማይችል ግልፅ ነው፡፡

የዜጎች መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶችን ከማረጋገጥ አንፃር የፍትህና የዲሞክራሲ አስተዳደር ተቋማቶቻችንን ለማጠናከር ለአመታት የተሰሩ ስራዎች እጅግ አናሳ ከመሆናቸውም በላይ፤ በየጊዜው እያደጉ ለመጡ የዴሞክራሲና የፖለቲካ መብቶች መሸራረፍም ዋና ምክንያቶች ነበሩ፡፡

ከዚህ ነባራዊ ሁኔታችን በመነሳትም የፍትህና የዲሞክራሲ ስርኣቱን በማበልፀግ ረገድ ቁልፍ ሚና የሚኖራቸውን ህጎች፤ ተቋማትና አሰራሮችን አንድ በአንድ እየለየን ተገቢውን የማሻሻያ እርምጃ የምንወስድበት ግዜ ነው፡፡

ህጎቹም ሆኑ ተቋማቱ – ህገ-መንግስታችንና አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ባስቀመጡት መንፈስና አቅጣጫ ብቻ ግባቸውን እንዲያሣኩና – በህዝብ አመኔታ የሚጣልባቸው ገለልተኛና ዘመን-ተሻጋሪ ተቋማት እንዲሆኑ ለማድረግም ሁሉን-አቀፍ የማሻሻያና የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

ይሁንና የፖለቲካ ማሻሻያዎችን ከኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ነጥሎ ማካሄድ – በረጅም ጊዜ ማእቀፍ ሲታይ – ዘላቂ ውጤት እንደማያመጣ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት – በኢኮኖሚ ዘርፉ አስፈላጊውን የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በመተግበር የአገራችንን ኢኮኖሚ ዘላቂ ዕድገት እናረጋግጣለን ፡፡
መንግስት የጀመረውን ሰፊ የዲሞክራታይዜሽን ስራ ከማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ እና ዘለቄታዊ ሰላም፤ የሕግ የበላይነት ፤ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ብልጽግና ለማረጋገጥ በበጀት አመቱ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ይሰራል፤

• ለዘመናት በመልካም ሆነ በፈታኝ የታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ አብሮነትና መቻቻል የአገራችን ህዝቦች አይነተኛ እሴት ሆኖ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የተጋረጠብን ትልቅ ፈተና ነጻነትንና ሥርዓት አልበኝነትን ባለመለየት፤ መረን የለቀቀ፣ ሕግና ሥርዓትን የማያከብር እንቅስቃሴዎችና ድርጊቶች መስፋፋት ነው።

እንዲህ ያሉት እንቅስቃሴዎች የዜጎችን ደህንነትና የአገሪቱን ሰላም በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑ ይገኛሉ። በዚህም የተነሳ ዜጎች ክቡር ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ለዘመናት ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ጥለው ተሰደዋል፡፡

በጥቅሉ የሕግ የበላይነት አደጋ ላይ ወድቋል፡ በህግ የበላይነት መርህ የማይመራ ሀገር እጣ ፈንታ ደግሞ የማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ መስፋፋት፤ ግጭት፤ ጥፋትና መበታተን ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት ይህንን ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የእያንዳንዱን ዜጋ ደህንነትና ነፃነት ለማስከበር አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ ይወስዳሉ፡፡

• የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የተጀመረው የሪፎርም ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓቱ እንዲጎለብትና እነዚህ መልካም ጅምሮች በዘላቂነት ተቋማዊ ቅርጽ ይዘው እንዲቀጥሉ በቀጣይነት የሕግ ማዕቀፉን ማሻሻልና የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር ብቸኛው አማራጭ ነው።

ይህንን ሂደት በአግባቡ ለመምራት ገለልተኛ የሆነ የሕግና ፍትህ አማካሪ ጉባዔ ተቋቁሟል። ይህ ጉባዔ በቴክኒክ ኮሚቴ የሚታገዝ ሲሆን በበጀት አመቱ የጸረ-ሽብር አዋጅ፡የሲቪክ ማህበራትና የበጎ አድራጎት አዋጅ፤ መገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ እና ሌሎችን የማሻሻሉ ስራ ይጠናቀቃል።

በተጨማሪም በሚዲያ ነጻነትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መከበር ዙሪያ የተጀመረው አበረታች ለውጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል። እዚህ ላይ አጽንኦት መስጠጥ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር የሚዲያ ተቋማትና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በማህበረሰባችን ያለውን መቻቻል እና አብሮ መኖር በሚያጠናክር ስሜት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ነው፡፡

• የምርጫ ሕጉ ስልጣን በሃይል ከሚያዝበት አዙሪት ወጥተን በሃሳብ ክርክር እና ልዕልና በሕዝብ ምርጫ ስልጣን ወደሚያዝበት ሰላማዊና የሰለጠነ ስርዓት የሚያሸጋገር የጨዋታ ህግ ስለሆነ መንግስት በልዩ ትኩረት ይመለከተዋል።

ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመመካከር የምርጫ ሕጉን ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ እንዲሆን የተጀመሩ የማሻሻያ ስራዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ ይደረጋል።

ስለሆነም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሃገራችንን ወደፊት ሊያራምዳትና እጣ ፈንታዋን ሊወስን በሚችለው የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ በሃላፊነት መንፈስና ሕግን ተከትለው አስተዋጾ እንዲያበረክቱ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የምርጫ አስፈጻሚ ተቋማትም በገለልተኝነት ስራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችሉ ተገቢ እርምጃዎችን እንወስዳለን ፡፡

• ባለፉት አመታት አገራችን በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ፖሊሲዎቻችና በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በመመራት፣ የመንግስትና የህዝብ አቅሞችን በማነቃነቅና በአይነቱ ትርጉም ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

ከዚሁ በተያያዘም የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ እና የዋጋ ንረትን በቁጥጥር ውስጥ ማስገባት የተቻለበት ሁኔታ ነበር፡፡ይሁን እንጂ ከቅርብ አመታት ወዲህ በአገራችን የተፈጠረው አሳሳቢ የሆነ አለመረጋጋት እንዲሁም በኢኮኖሚው ውስጥ ስር እየሰደዱ የመጡ የውጪ ምንዛሬ ዕጥረት፣ የሃይል አቅርቦት፣የሎጂስቲክስ፣ የታክስና የመንግስት አገልግሎት የቅልጥፍና ችግሮች ምክኒያት የኢኮኖሚ ዕድገታችን ፍጥነት ትርጉም ባለው ደረጃ እንዲቀንስ አስገድደውታል፡፡

• በግብርና ላይ የተመሰረተው ኢኮኖሚያችን በሚፈለገው ፍጥነት በአምራች ኢንደስትሪ ዘርፍ ላይ ወደተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ካለመሸጋገሩም በተጨማሪ፤ የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገትም ቢሆን በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው የህዝባችን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና የወጣቶች ስራ-አጥነትን ጥያቄ ጋር ሳይጣጣም ቆይቷል፡፡

በመሆኑም በተለይ ለወጣቱ የማህበረሰብ ክፍል ከቀረፅነው የስራ ፈጠራ መርሀ-ግብር ጎን ለጎን፤ የኢኮኖሚ ምህዳሩን የበለጠ በማስፋትና የግል ዘርፉን ተሳትፎ በማሳደግ እና ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ተጨባጭ የማሻሻያ እርምጃዎችን እንወስዳለን፡፡ በእርግጥም 65 በመቶ የሚሆነው የአገራችን ሕዝብ ወጣት ከመሆኑ አንጻር የስራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳ ከብሔራዊ ደህንነታችን ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግስታችን ሳይታክት ይህንን አጀንዳ ከግብ ለማድረስ የሚተጋው፡፡

• የባለፉት ሶስት የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜን እቅድ በጀት አመታት እቅድ አፈፃፀም በአገር ውስጥ በተፈጠርው አለመረጋጋት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሀገራችን ተከስቶ በነበረው አስከፊ ድርቅ እና በአለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የሸቀጦች የገባያ ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ ተፅዕኖ ስር በመውደቁ ውጤቱ የመዋዥቅና የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል፡፡

• በአገራችን ተፈጥሮ የነበረው የሰላም መጥፋትና አለመረጋጋት እንዲሁም እያደገ የመጣው ስር የሰደደ የኢኮኖሚ ችግሮች ባለሃብቶችን ተስፋ ያስቆረጠ እና ዘገምተኛ የንግድ ስራ ውሳኔ አስጣጥ ሂደትን በማስከተሉ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማሽቆልቆል እዲገታና በአጠረ ጊዜ ወደ መደበኛው ፈጣን እድገት ለማምጣት የሚያስችል የማገገሚያ (revitalization) ፖሊሲ መተግበር ይጠይቀናል፡፡
በዚህ ረገድ መንግስት በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚወስዳቸው እርምጃዎች: –

• በዚህ በጀት አመት የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ነፃ ገበያ ስርዓትን በመገንባት፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚውን በቀጣይነት ለማረጋገጥ እና የማህበረ- ኢኮኖሚ ልማትን ለማበረታታት ተስማሚ ሁኔታ እንዲፈጠር አበክረን እንሰራለን፡፡

የነፃ ገበያ ህግጋትን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር እንዲሁም በአለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትስስር ያለንን ቦታ ለማሻሻልና ፍትሃዊ ውድድርን፣ እኩልነትንና ግልፅነትን በእያንዳንዱ አካባቢና ኢንዱስትሪ ለማረጋገጥ የሚያስችለንን ዝግጁነት እናጠናክራለን፡፡ የገንዘብ ፖሊሲ፣ የፊስካል ፖሊሲ እና ሌሎች ፖሊሲዎችን በማጣመር የማክሮ ኢኮኖሚውን የማረጋጋትና የኢኮኖሚውን ሚዛን ለማስጠበቅ ጠንካራ ስራ ይስራል፡፡

ስትራቴጂክ የእድገት እርምጃዎችንና ስር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥን ፈጠራና ቴክኖሎጂ ላይ በተመሰረተ የዕድገት ሞዴል እንዲሁም ምርታማነትን፣ቅልጥፍና እና ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል የሚደረጉ ትግበራዎች እንዲፋጠኑ ይደረጋል፡፡

• የመንግስት ገቢና ወጪ አስተዳደር ህግን መሰረት አደርጎ በቁጠባና በውጤታማነት እንዲፈፀም፣ የታክስ ገቢ አስባሰብ ስርዓትን የሚያጠናከር፣ የታክስ ብክነትን በበቂ ሁኔታ የመከላከል እና ውዝፍ የታክስ ገቢን የሚቀንሱ ስራዎችን ትኩረት አግኝተው እንዲፈፀሙ ይደረጋል፡፡የመንግስት ገቢና ውጪን አወቃቀር በማስተካከል ለልማት የሚውለው ኢንቨስትመንት መጠን እንዲያድግ ይደረጋል፡፡

አገራችን በብድር የምታገኘውን ሀብት በጥብቅ የመቆጣጠር ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል እንዲሁም የአገራችን ብድር በአጠቃላይ ሆነ የመንግስት ብድር ከተቀመጠለት ጣራ በላይ እንዳያልፍ በጥብቅ የማረጋገጥ ስራ ይሰራል፡፡

• ብድር አስተዳደሩንና አጠቃቀሙን ውጤታማነት የማሻሻልና በመንግስት ዋስትና የሚሰጡ ብድሮችንና ብድርን ለመክፈል የሚሰጡ ብድሮች ደረጃ በደረጃ እንዲቀንሱ ይደረጋል፡፡

• የፐብሊክ ኢንቨስትመንት አስተዳደርንና ቅልጥፍናን የማሻሻል ስራ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡ የመንግስት ፋይናንስ ከመንግስት ሴክተር ውጪ የሆኑ ኢንቨስትመንቶችን ለማሳደግ በሚያስችል መንገድ አሰራሩ ይሻሻል፡፡

የፋይናንስ ገበያውን አወቃቀር የማሻሻያ ስራዎችን በመስራት በገንዘብ ገበያ፣ በካፒታል ገበያ እና በኢንሹራንስ ገበያ መካከል ተገቢ መስተጋብር እንዲኖር የሚያስችል ስራ ይሰራል፡፡

የተለያዩ የኢንሹራንስ ተቋማትን አፈፃፀም ቅልጥፍ የማሻሻልና የኢንሹራንስ ሽፋን የማሳደግ ስራ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ የአበዳሪ ተቋማት የተበላሹ ብድሮችን ለማስተካከል፣ የባንክ ስርዓትን ደህንነት ለማረጋገጥና አለም አቀፍ የባንክ አስተዳደር ሰታንዳርድንና ልምድን ለመተግበር የሚስችል ቁመና እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡

• በቅርብ ግዜ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተረታ ለመሰለፍ ያለንን ግብ ግምት ውስጥ ያስገባ፤ አስተማማኝ የውጭ ንግድ ሁኔታ ማመቻቸት የመንግስታችን ቁልፍ ተግባር ይሆናል፡፡

በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ለምታመርታቸው ምርቶች አስተማማኝ የገበያ መዳረሻዎችን የሚያመቻች ፤ ሀገራችንን ከአካባቢያው ትስስር ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችልና የአለም አቀፍ የንግድ ትስስር አካል በማድረግ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆን የሚያስችል የንግድ ድርድሮች በአዲስ መንፈስና ጥረት ዳር ለማድረስ ሰፊ ስራ ይሰራል፡፡

በተጨማሪም በረጅም ጊዜ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ታሳቢ ያደረገ በመካከለኛ ጊዜ ግን ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትስስርንና ውህደትን ማሳካት እንዲቻል መንግሥታችን ወጥና የተቀናጀ የንግድ ፖሊሲና ድርድር በማካሄድ ቀዳሚ ሚና ይጫወታል። የድንበር አካባቢ ንግድ ህግና ስርዓትን ተከትሎ እንዲከናወን ይደረጋል፡፡ ይህም ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሻገር በቀጠናው እየተፈጠረ ያለውን ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ያደርገዋል።

• በዚህ ረገድ በተለይም ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣንን (ኢጋድ) በማጠናከርና ወደ ዘላቂ ልማት በሙሉ ሃይልና ትኩረት እንዲገባ በማድረግና የአካባቢያዊ ኢኮኖሚ ትስስርን እንዲጠናከር መንግስታችን የመሪነት ሚናውን ይወጣል፡፡

 

• በአፍሪካ ደረጀም ቢሆን የአቡጃ ስምምነትን መሰረት በማድረግ አህጉር አቀፍ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመመስረት እየተደረገ ባለው ድርድር ንቁ ተሳትፎ እንዳርጋለን፡፡

ከዚህ በተያያዘ በአህጉራችን ያለውን ነጻ የሕዝቦች እንቅስቃሴ እንዲጎለብት የአፍሪካ ህብረት በቀረፀው ፕሮግራም መሰረት ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የመድረሻ ቪዛ መስጠት የሚችሉበት ጊዜ እ.ኤ.አ 2023 እንዲሆን ያስቀመጠ በመሆኑ ኢትዮጵያም የሕብረቱ መቀመጫ እንደመሆኗ ለአፍሪካ ሃገራት ዜጎች የመድረሻ ቪዛ መስጠት ትጀምራለች፡፡

ይህም ለኢኮኖሚ ትስስሩ አጋዥ ከመሆኑም ባለፈ አገራችን ያላትን የቱሪስት ፍሰት ለመጨመር በተለይም ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድገት በእጅጉ እንዲያግዝ ያስችላል፡፡ በተጨማሪም የቪዛ ሥርዓታችንን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ እርምጃ እየወሰድን እንገኛለን፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ሌሎች የአለም አቀፍ ተቋማትና የዲፕሎማቲከ ማዕከል በመሆኗ መዲናችን አዲስ አበባ የምታስተናግዳቸው ኮንፈረንሶች ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመሩ ይገኛል፡፡

ለአፍሪካ አገራት ዜጎች የሚሰጠው የመዳረሻ ቪዛ ሥርዓትም ይህንን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል የሆናል፡፡

• ከንግድ ፖሊሲያችን የተያያዘው ሌላው አበይት ጉዳይ የአገራችን የዓለም የንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደትን የሚመለከተው ነው፡፡ አገራችን የአባልነት ጥያቄ አቅርባ ድርድር ከተጀመረ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘምን ሊጠናቀቁ ከሚገባቸው ተግባራት አንዱ ይኸው የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ነው፡፡

በመሆኑም ተገቢውን ድርድር በፖለቲካ አመራሩ ቅርብ ድጋፍ የአገራችንን ጥቅም ባስጠበቀ ሁኔታና በተቀናጀ አሰራር ሂደቱን ከግብ ለማድረስ ይሰራል፡፡

• የኢኮኖሚው ስር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥን ለማረጋገጥ የግብርናውን ዘርፍ የምርት አወቃቀር መሰረታዊ ለውጥ ውስጥ እንዲገባ ማድርግ ይጠይቃል፡፡

በዚህም መሰረት የግብርና የማምረት ቅልጥፍና የማሻሻልና አዳዲስ የገጠር ልማት እንቅስቃሴዎችን የማሳደግ ስራ ላይ ትኩረት በመስጠት የአርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ህይዎት የሚያሻሽሉ ተግባራት በትኩረት የሚፈፀሙ ይሆናል፡፡

የግብርና የአመራረት ስርዓት ኮመርሺያላይዜሽንን በሚያፋጥን ደረጃ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅሙ ኢንዲያድግ፣ የዘመናዊ የመስኖ መሰረተ ልማት ተደራሽነት እንዲሰፋ፣ በማሽነሪ ላይ የተመሰረተ ግብርና እንዲኖር በተቻለ መጠን ትኩረት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡

የመስኖ ልማትን በማስፋፋት እና የዘመናዊ ግብዓቶችን አቅርቦት በማሻሻል የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት እናሻሽላለን።

• የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን የስራ ስምሪትና የመሬት አጠቃቀም ዝቅተኛ ምርታማነት ካላቸው የግብርና ምርቶች ከፍተኛ ምርታማነት ወደአላቸው የግብርና ምርቶችን ለማምርት የሚያስችለን ሽግግር እንዲፋጠን አሰራሮቻችንን የመፈተሸና የክትትልና የድጋፍ ስራችን የማጠናከር ተግባራት በትኩረት ይሰራል፡፡

የግብርና ምርትና ሽቀጦች የገበያ ተወዳዳሪነት ትርጉም ባለው ደረጃ የማሻሻል ስራ በሁሉም የእሴት ሰንሰለት ይተገበራል፡፡ የገጠር ኮመርሺያላይዜሽንን ለማስፋፋት የሚያስችል የመሬት ስብስብን የሚያበረታታ ተስማሚ ፖሊሲን በመቅረፅ እንዲተገበር ይደረጋል፡፡

• ከዚህም በተጨማሪ በከፍተኛ ስኬል የግብርና ማምርት ስራዎችን ለመስራት በአገራችን ተስማሚ በሆኑ አካባቢዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እያደገ የመጣውን ህዝብ የምግብ ፍላጎትና የኢንዱስትሪ ግብዓት የመሸፈን ስራ ይሰራል፡፡ጠንካራ የህብረት ስራ ማህበራት እና የቤተሰብ የንግድ ስራ ኢንተርፕራይዝ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት መስኮች በገጠር አካባቢዎች እንዲቋቋሙና ኢንዲስፋፉ ይደረጋል፡፡

• የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ለማሻሻል የተለያዩ የፖሊሲ፣ የሕግ እና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ በዘርፉ የሚታየውን ጉልህ የገንዘብ አቅርቦት ችግር በመሰረታዊ መልኩ ለመፍታት ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን፤ የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ለውጥ ለማሳካት የመንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርክ ስትራቴጂ በአግሮ-ኢንዱስትሪ ላይ ባተኮረ መልኩ ይቀጥላል።

• ሰፊና አስተማማኝ የስራ ዕድል መፍጠር የመንግስታችን ትልቅ አጀንዳ ነው፡፡ የስራ ዕድል ፈጠራ አስተማማኝ የሚሆነው የግል ዘርፉ ሲስፋፋና ሲጠናከር መሆኑ እሙን ነው፡፡ የመንግስት ዋና ሃላፊነት የግል ዘርፉ ያሉበትን ችግር በመለየት ተገቢውን የማሻሻያ እርምጃ በመውሰድ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን መፍጠርና በአጋርነት መንፈስ ለመስራት ማበረታት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የግል ዘርፉ ዕድገት በመንግስት ከልክ ያለፈና ያልተገባ የቁጥጥር፤ የሕግ፤ የአስተዳደርና የአሰራር ማነቆ እንዳይሸበብ ለማድረግ ዘመናዊ የንግድ እንቅስቃሴን ለማስፈን የሚያስችሉ የሕግ ማሻሻያዎችን ይተገብራል፡፡

ለአብነትም ከሁለት አስርት ዓመታት ላላነሰ ጥረት ሲደረግበት የቆየውን የኢትዮጵያ የንግድ ሕግን የማሻሻል ሂደት በበጀት አመቱ አጠናቆ ለተከበረው ምክር ቤት እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴን የሚደግፉ አዲስ የኢንቨስትመንት ሕግ፤ ዘመናዊ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ይጠናቀቃሉ፡፡

የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰራርን በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ቀላል፤ ቀልጣፋና፤ ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ የጀመርነውን የሪፎረም ስራ አጠናክረን እንገፋበታለን፡፡ በተመሳሳይም የጉምሩክ እና የግብር ሥርዓታችንን ለማዘመን የተጀመረውን ስራ ከግብ ለማድረስ እርብርብ እናደረጋለን፡፡ በተለይም የጉምሩክ ሥርዓትን ለመፈጸም የሚያስችል የኤሌክትሮኒክስ የአንድ መስኮት አገልግሎት በማጠናቀቅ ወደ ስራ እንዲገባ ይደረጋል፡፡

• የውጭ እና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በከፍተኛ ቁጥርና ጥራት ከመመልመል፤ ወደ ልማት እንዲገቡ ከማድረግና ለኢንዱስትሪዎች የሚፈለገውን አምራች የሰው ሃይል ከማዘጋጀት ጎን ለጎን በመንግስት ባለቤትነት ተይዘው የነበሩ ግዙፍ የልማት ድርጅቶች በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ ወደግል ባለሀብቶች ለማዘዋወርና-መንግስትም በገበያው የሚኖረውን ድርሻ በመቀነስ የግል ዘርፉን ተሳትፎ በማሳደግ የኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂነት ለማረጋገጥ ሰፊ ስራ ይሰራል፤

• ቅድሚያ ከተሰጣቸው የኢንቨስትመንት መስኮች በተጨማሪ መሬትን በባለቤትነት በካፒታል ድርሻ በመያዝ በተመረጡ ከተሞች ትላልቅ የጋራ ልማት ኢንቨስትመንቶች እንዲካሄዱ በማድረግ ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርም ሆነ ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ ልማቱ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ይደረጋል፣

• አገራችን ያጋጠማትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ለመቅረፍ ከምንወስዳቸው ሰፋፊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሪፎርሞች በተጨማሪ የአገራችን ኤክስፖርት ለማስፋፋት በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በጥናት በመለየት ተገቢውን የማሻሻያ እርምጃ እንወስዳለን፤ በተለይ ጎልቶ የሚታየውን የሎጂስቲክስ ዘርፍ ተወዳዳሪና ውጤታማ ያለመሆን ችግር ለመቅረፍ የተቀናጀ ስራ ይሰራል፡፡

• የዳያስፖራው ተሳትፎ አንድ ዶላር በቀን ከሚለው አጋርነት ጀምሮ በተለያዩ አጋርነቶች እንዲጠናከር ይደረጋል፣

• በሰሜን አሜሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ የተጀመሩት የዳያስፖራ ተሳትፎ የማጠናከር እና የዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በአውሮፓም እንዲጠናከር ይደረጋል፣

ሌላው ትኩረት የሚያሻው ትልቁ ጉዳይ የትምህርት ዘርፍ እንደሀገር ለማሳካት የተጣለው ግብ እንደተጠበቀ ሆኖ በያዝነው አመት በተለይም ለአዲሱ የፍኖተ ካርታ መሰረት የሚሰራ ይሆናል፡፡ ምንም እንኳን መንግሥት የትምህርትን ተደራሽነት በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ስኬት ያስመዘገበ ቢሆንም የትምህርት ጥራት ግን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል።

ይህንንም ከመሠረቱ ለመቀየር በየደረጃው አስፈላጊው የሪፎርም ሥራ ይሠራል። በሁሉም ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ያለምንም የጸጥታ ስጋት ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

በጤናውም መስክ እንደሀገር ያስመዘገብናቸው አያሌ ስኬቶች ቢኖሩም አሁንም የተደራሽነት ደረጃና ጥራት ያለው አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ሰፊ ክፍተት በመኖሩ በያዝነው በጀት ዓመት የሕፃናትና የእናቶች ሞት በከፍተኛ ቁጥር ለመቀነስ ብሎም የመሠረታዊ ጤና አገልግሎትና የሆስፒታል ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ ይሆናል፡፡

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት፥
በያዝነው የበጀት ዓመት መንግስት በዜጎች ተዓማኒነት ያላቸው ተቋማት እንዲኖሩና ያሉትም እንዲጠናከሩ በርካታ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ በዚህ ረገድ ተግባራዊ ከሚደረጉት ቀዳሚ ተግባሮቻችን መካከል አንዱ የፌደራል አስፈጻሚ አካላት አወቃቀር ማሻሻያ ነው። መንግስታዊ ተቋማት ግልጽ ዓላማ ያላቸው፣ በቅንጅት የሚሰሩ፣ ውጤታማና ወጪ ቆጣቢ እንዲሆኑ ለማድረግ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶችን በጥልቀት በማጥናት ተገቢውን ማሻሻያ በማድረግ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ያጠናቀቀ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥም ለተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል።
የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት፥

በሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስር እንዲሰድና ዜጎችም ከትሩፋቱ መጠቀም እንዲችሉ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ሠላማዊ መንገድና አቅጣጫን የተከተለ እንቅስቃሴን በቃልም በግብርም መርጠው መጓዝ ይኖርባቸዋል፡፡ አዲሱን ለውጥ ተከትሎ በየአካባቢው የታዩ ግጭቶች ፣የተስተዋሉ መፈናቀሎች ፣ሞትና ስደቶች አሳሳቢና ፈጥነን መፍትሄ ልንፈልግላቸው የሚገቡ መሆናቸው የሚካድ አይደለም፡፡ እነዚህ አሳዛኝ ገጠመኞች ተስፋ ሰጪ እውነታ በውስጣቸው ያኖሩም ነበሩ፡፡ በእነዚህ አለመግባባቶች ውስጥ እንኳ በህዝቦች መካከል የተስተዋለው የመደጋገፍና የመረዳዳት ሁኔታ አንድነትና ሕብረታችንን የይስሙላ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ገፅታ መላበሱን ሀገራዊ አንድነታችንም ተጠናክሮ የሚቀጥል በህዝቦቻችን መካከልም ጊዚያዊ እንጂ መሠረታዊ ቅራኔ አለመኖሩን የመሰከረ እውነታ ነበር፡፡ ለአብነትም የጋሞ አባቶች በቅርቡ ሊፈጠር የነበረን ግጭትና ጉዳት ለዘመናት ባቆዩት ባህላዊ ዕሴት የታደጉበት ተግባር ሁላችንንም እንደ ኢትዮጵያዊ ያኮራ ነበር።

የዚህ ዓመት ቀጣይ ትኩረት ፍቅርና እርቀ-ሠላምን ፤ መደመርና አንድነትን የሚያስቀጥል ዓመት እንዲሆን ሁላችንም በሆደ-ሠፊነት መሥራት ይኖርብናል፡፡ ዜጎቻችንም ለሕግ የበላይነት ዘብ እንዲቆሙ እያሳሰብኩና አዲሱ ዓመት የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት መልካም የሥራና የስኬት ዘመን እንዲሆንላችሁ መልካም ምኞቴን እየገለፅኩ የ2011 የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን በይፋ መከፈቱን አበስራለሁ።

አመሰግናለሁ!!

You might also like
Comments
Loading...