Fana: At a Speed of Life!

ጥያቄያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ጉዳይ በቅርበት ያልተከታተሉ አመራሮችን የመለየት ስራ ይሰራል – የመከላከያ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 2 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተገኝተው ጥያቄያቸውን ያቀረቡ የኢፌዴሪ የመከላከያ ማዕከል ግብረ ሃይል 2ኛ ክፍለ ጦር ሬጅመንት አባላትን ጥያቄዎች በቅርበት ያልተከታተሉ አመራሮችን የመለየትና የማጣራት ስራ እንደሚሰራ የመከላከያ ሚኒስትሩ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ከሬጅመንት አባላቱ ጋር ከተደረገው ውይይት ማጠቃለያ በኋላ በሰጡት መግለጫ፥ የሬጅመንት አባላት ጥያቄያቸው ትክክለኛ እና ተገቢ ቢሆንም ጥያቄያቸውን ያቀረቡበት መንገድ ግን የተሳሳተና ህግና ደንብን የጣሰ ነው ብለዋል።

የመከላከያ ሃይል አባላቱ ለአንድ ወር የዘለቀ ግዳጅ ካጠናቀቁ በኋላ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማነጋገር እንፈልጋለን በማለት በቀጥታ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት መሄዳቸውንም በመግለጫቸው አንስተዋል።

አባላቱ እንዴት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት እንደሄዱ፣ ጉዳዩን የመከላከያ ሚኒስቴር የበላይ አመራሮች ያውቁ ነበር ወይ? ለምንስ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከመድረሳቸው በፊት ማወያየት አልተቻለም የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

በምላሻቸውም ሂደቱን በቅርበት ያልተከታተሉና ምላሽ ያልሰጡ የአመራር አባላትን የመለየትና የማጣራት ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

የመከላከያ ሃይሉ ስነ ምግባርና ህግ አክባሪነትን በተመለከተ ሰራዊቱ በጥብቅ ስነ ምግባር የሚመራና በህግ የበላይነት የሚያምን በመሆኑ የሃገሪቱ ህዝቦች ተመሳሳይ ሁነቶች ይከሰታል የሚል ስጋት እዳይገባቸው ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

 

 

በዳዊት መስፍን

 

You might also like
Comments
Loading...