Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ባለድርሻ የሆነችበት የበርበራ ወደብ ማስፋፊያ ግንባታ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 2 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ 19 በመቶ ባለድርሻ የሆነችበት የሶማሊላንድ በርበራ ወደብ የማስፋፊያ ግንባታ ተጀመረ።

የወደቡ ማስፋፊያ ግንባታ በትናንትናው እለት የተጀመረ ሲሆን፥ በስነ ስርዓቱ ላይም የሶማሊ ላንድ አስተዳደር፣ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች እና የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የማስፋፊያ ግንባታው በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶቹ ዱባይ ፖርት ኩባንያ አማካኝነት የሚካሄድ ይሆናል።

ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ላይ 19 በመቶ ድርሻ ሲኖራት፥ የሶማሊ ላንድ አስተዳደር 30 እንዲሁም የዱባይ ፖርት ኩባንያ 51 በመቶ ድርሻን ይይዛሉ።

የወደቡ ማስፋፊያ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ የወደቡን የማስተናገድ አቅምም በ50 በመቶ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ወደቡን ከኢትዮጵያ ጋር ለማገናኘትም የ100 ሚሊየን ዶላር የመሰረተ ልማት ግንባታ ማካሄድ የሚያስችል ውይይትም እየተካሄደ ነው ተብሏል።

የሶማሊ ላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የበርበራ ወደብ ለኢትዮጵያ አማራጭ ወደብ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በርበራ ለኢትዮጵያ አማራጭ ወደብ ከመሆን ባለፈም ኢትዮጵያን ከደቡብ ሱዳን እና መካከለኛው አፍሪካ ጋር ለማገናኘት ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የተናገሩት።

ፕሬዚዳንቱ የበርበራ ወደብ ግንባታ የሶማሊ ላንድን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ለቀጠናው የንግድና ኢኮኖሚ ትስርስር ከፍ ያለ ሚና ይጫወታልም ብለዋል።

 

 

 

ምንጭ፦ somalilandsun.com/

 

 

You might also like
Comments
Loading...