Fana: At a Speed of Life!

ለዘረኝነት ማበብ ማህበረሰባዊ ሞራላችን እየተሸረሸረ መምጣት ተጠያቂ ይሁን?

”በፖለቲካዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ መስክ እንደ ሃገር እያጋጠሙን ያሉት ቀውሶች መንስኤ ብቻ ሳይሆን ማስተካከያ መፈትሄውም በብዙ ገፅታው ከተላበስነው ወቅታዊ የሞራልና የግብረ ገብነት ደረጃ ጋር የተሰናሰለ ነው።” ይህ ንግግር ባለፈው ሳምንት 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ በሃዋሳ ሲከፈት የግንባሩ ሊቀ መንበር እና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ካደረጉት ንግግር ላይ የተቀነጨበ ነው። ንግግሩ ሃገራዊ ነባራዊ ሁኔታውን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ስለመሆኑ አያጠራጥርም።

”ዝርፊያና ሌብነት፤ ጥላቻና ቂመኝነት፤ ዘረኝነትና ስግበግብነት ምንጫቸው የሞራልና የግብረ ገብ ደረጃ መዝቀጥ መሆኑ አያጠያይቅም።” ይላሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው ላይ፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ማህበረሰባዊ ሞራልና ግብረ ገብ ይፈልጋል በማለት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ መምህር የሆኑት ዶክተር ታየ ንጉሴ ማህበረሰባዊ ሞራል ምን ማለት እንደሆነ ሲያበራሩ “ሁሉን አቃፊ፤ ሁሉን በእኩል የሚያይና መከባበርን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ” ሲሉ ያስቀምጣሉ።”የሞራል እሳቤዎች  ለምሳሌ ያህል አቃፊነት፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ከሌሎች ጋር አብሮ መኖር፣ ሌሎችን መርዳት የመሳሰሉት እነኝህ ማህበራዊ እሴቶች ናቸው የሞራል እሴቶች የምንላቸው።” ይላሉ።

እንዲህ አይነትን የሞራል ልዕልና ላይ የደረሰ ማህበረሰብ የሚመራው በህግና ህግ ብቻ ይሆናል። ዴሞክራሲያዊ ሰርዓት ለመገንባትም አያስቸግርም። በተቃራኒው የሞራል ዝቅጠት ሲያጋጥም ግዴለሽ የሆነ ማህበረሰብ ይፈጠራል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ እንደሚሉት፥ ሞራልና ግብረ ገብ የሌለው ማህበረሰብ ከራስ አልፎ ሃገርንም ጭምር ፈተና ውስጥ የሚከት ነው የሚሆነው። ”የሞራል መዝቀጥ ወይም መውደቅ አንዱ ከግለሰብ ይጀምራል። ግለሰቡ ለራሱ ክብር አይሰጥም፤ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከብር አይሰጥም፤ ለሃገር አድገት ህልውና ብዙም ደንታ የለውም፤ ስለዚህ ደንታ ቢስ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ ይሄዳል፤ ደንታ ቢስ በሆነ ትውልድ የሚሞላ ሃገር ከሆነ ሃገር እንደ ሃገር መቀጠል በራሱ ችገር ነው የሚሆነው።” ሲሉ ያስረዳሉ።

ዛሬ እንደ ሃገር ኢትዮጵያን እየተፈታተናት የሚገኘውም ከዚህ የሚመነጭ ይመስላል። ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይጠይቃል። ስርዓቱን ለመገንባት የሚያስችል ማህበረሰባዊ የሞራል ልዕልና ግን የቀጨጨ መሆኑ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሃዋሳው ንግግራቸው አስረግጠው የተናገሩትም ይህንኑ ነው። ”የስራ ፍቅርን፣ የሰው ክቡርነትን፣ ፍትህን ፣ዴሞክራሲያዊ አመለካከትን፣ የሃሳብ ልዕልናን እንዲሁም ሰላምና እኩልነትን የማስረፅ እና የማረጋገጥ ሂደት በሞራልና በግብረ ገብ ደረጃው በወደቀ ማህበረሰብ ውስጥ የሚታሰብ አይደለም።”

በስነ ማህበራዊ ጥናት የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የኢኮኖሚ፣ የቤተሰብና የትምህርት ተቋማት የሚባሉ አምስት ማህበራዊ ተቋማት አሉ። እነዚህ ተቋማት ተያያዥና ተደጋጋፊ ናቸው። አንዱ ላይ የተበላሸ ስርዓት ወደ ሌሎቹም ተዛምቶ ይወራረሳሉ። ሞራላዊ ሰርዓትም ሆነ ስነ ምግባር ያለው ዜጋ በመፍጠር ዘንድም ያላቸው አስተዋፅኦ እነዚህ ተቋማት ከፍተኛ ነው።

ዶክተር ታየ እንደሚሉት አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው አክራሪ ብሄርተኝነት የሚመነጨው ከፖለቲካ ተቋማት ብልሽት የሚመነጭ ነው። ብሄርተኝነትና ዘረኝነት ጫፍ የረገጡ ሁነዋል። ብሄር እየለዩ በየአካባቢው የታዩት መፈናቀሎች ለዚህ የሞራል ዝቅጠት ማሳያ ሊሆን ይችላል።

በዚህ ምክንያት ከሃገራዊ ልዕልና እየተሸረሸረ መጥቶ ክልላዊ ልዕልና እየነገሰ መጥቷል ባይ ናቸው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ዜጎች የሚለኩትም በሰውነታቸው ሳይሆን በብሄራቸው እየሆነ መጥቷል የሚሉት ምሁራኑ፥ የሁለት ግለሰቦች ፀብ ብሄር ተኮር የመሆኑ ምክንያት ከዚሁ ከማህበራዊ የሞራል እሴት ማሽቆልቆል ጋር ይገናኛል ይላሉ ዶክተር ዮሃንስ ሃድገ።

”ሰውን በሰውነቱ ብቻ ካላየንና የምተገባውን ሽልማት፤ የሚገባውን ቅጣት ነፃና ገለልተኛ ሁነን መስጠትና መመዘን ካልቻልን አይደለም ዴሞክራሲ በሰላም ህይወታችንን ስለማቆየታችንም አደጋ ላይ ነው ፤ ምክንያቱም ዘረኝነቱ በሙሉ ሌላው ነገር ሁሉ ድምጥማጡን ነው ያጠፋው።” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።

ማህበረሰባዊ የሞራል ዝቅጠት ባገጠመው ሃገር ውስጥ ስግበግብነት ያይላል፤ብሄርተኝነትና ዘረኝነት ባየለበት ሃገር ውስጥ ደግሞ የህግ ተጠያቂነትም ልል እንዲሆን በማድረግ አስተዋፅኦው የጎላ ይሆናል።

ይሄ ሂዶ ሂዶ ደግሞ ግለሰቦች ብሄራቸውን ሽፋን አደርገው ህዝብን እንዲበዘብዙ ምክንያት መሆኑ አይቀርም።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሞራልና የስነ ምግባር ተሃድሶ የሚያስፈልግበት ወቅት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንደተናገሩት፥ ዜጎች ማህበራዊ የሞራል እሴቶቻቸው ላይ እድሳት ማድረግ ካልተቻለ የታሰበውን የዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት አይቻልም። ”በይቅርታና በእርቀ ሰላም፤ በፍቅርና በመደመር መሻገር የምንሻ ከሆነ አሰቀድመን የህሊናና የሞራል ተሃድሶን እንደ ግለሰብ እንደ ማህበረሰብና ህብረተሰብ የማረጋገጥ ሃላፊነታችንን በሚገባ መወጣት ይኖርብናል።”  ሲሉም ነው በንግግራቸው ያነሱት።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ታዲያ አሁን መፍትሄ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ መቅደም ያለበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ቤተሰባዊና የትምህርት ተቋማት ራሳቸውን ማፅዳት ሲችሉ ነው ይላሉ ዶክተር ታየ።”ትምህርት ቤታችን ዝም ብሎ ሌላ የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ከሆነ ሃይማኖቱም የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ መንዣ ከሆነ ኢኮኖሚውም እንደዛ ከሆነ እንዴት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ተቋማት ራሳቸውን ማፅዳት አለባቸው። ራሳቸውን ካፀዱ በኋላ ከዛ ማህበረሰባዊ ሃላፊነታቸውን ይወጣሉ።” ይላሉ ምሁሩ።

የሃገሪቱ ፖለቲካም ከጥላቻ ወጥቶ በመከባበር ላይ ተመሰርቶ በሃሳብ የሚፎካከርበት መድረክ ሊኖር ይገባልም ይላሉ፤ ”ጤናማ የሆነ ግንኙነት በህብረተሰቡ መካከል ይኖራል፤ ዘረኝነትን የሚያስፋፉ ፤ የጥላቻ ቅስቀሳዎችን የሚያርሙ የሚያወግዙ መሆን መቻል አለባቸው፤ የእነሱ ብሄር አባል ስለሆነ ብቻ መጥፎ ስራ እየሰራ እያዩ ዝም ማለት የለባቸውም፤ ስልጣን ላይ ሆኖ የሚያበላሽ ነገር ካለ እኛን አየወክልም ብሎ በጊዜው ማረም ማንሳት በጣም አስፈላጊ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፤ የለም የአንተ ሃሳብ ትክክል አይደለም ብሎ መጨፍለቅም ተገቢ አይደለም፤ እንዲህ ባለበት ሁኔታ ዴሞክራሲ ሊታሰብ አይችልም።” የሚልም ሀሳብ ሰንዝረዋል።

ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ትምህርት ቤቶችና ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች ሁሉም ማህበረሰባዊ የሞራል እሴቶችን ማነፅ እንዳለባቸውም ይመክራሉ።

ያኔ በሃገሩ የሚኮራ፣ የሞራል ልዕልናው ከፍ ያለ፣ መልካም ምግባር ያለው፣ ኢትዮጵያዊ  በኢትዮጵያ መፈጠር ይቻላል። ያኔ መከባበርን መሰረቱ ያደረገ፤ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት መገንባት ይጀምራል።

 

በታደሰ በዙዓለም

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

You might also like
Comments
Loading...