Fana: At a Speed of Life!

ለነገ ትውልድ የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት የሁላችንም ሃላፊነት ነው – ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 21 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) ለነገ ትውልድ የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው እለት በጀርመን ፍራንክፈርት ኮሜርዝ ባንክ አሬና ስታዲየም ከተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ለመጡ ኢትዮጵያውያን ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም ለነገው ትውልድ የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት የሁላችንም ሃላፊነት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሃገራት ጋር ዘመን ተሻጋሪና ታሪካዊ ትስስር ነበራት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህም ለዛሬው ግንኙነት መሰረት መጣሉን አንስተዋል።

አውሮፓውያን በቀደመው ዘመን ያደርጉት የነበረውን የእርስ በርስ መሸናነፍ በመተው ድህነትን ማሸነፍ በመምረጥ አሁን ላይ የደረሱበት ደረጃም ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትምህርት እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አሁን ላይ ነጻነት እና ተስፋ በእጃችን መኖሩን ጠቅሰው፥ የምናስባትን ኢትዮጵያን ለመገንባት በልዩነት ሳይሆን በአንድነት መንፈስ መስራት ይገባናል ብለዋል።

ወቅቱም ዘረኝነትና የበላይነት መንፈስን በማስወገድና ከመገፈታተር አንድነትን በማምጣት እንደሃገር ጥርሳችንን ነክሰን የምንሰራበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

“ኢትዮጵያ ማንም በየጊዜው እየተነሳ በፍላጎቱ እንደ ቂጣ ጠፍጥፎ የሚሰራት የግል ርስት ሳትሆን፥ ዘመናትን ያስቆጠረች፣ ታላቅ ህዝብ የመሰረታት ታላቅ ሃገር” ናት ብለዋል በንግግራቸው።

ከዚህ አንጻርም ተስፋ ሳንቆርጥ፣ ሳንከፋፈልና በማይጠቅም ነገር ላይ ጊዜን ሳናጠፋ ከሰራን ኢትዮጵያን ዳግም ታላቅ ማድረግ እንችላለንም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያዊነትን ከቃላት ባለፈና ከስሜት በዘለለ በተግባርና በስራ የምንገልፅበት ወቅት ላይ ነን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከትናንት አያሌ መልካም ነገሮች ወስደን ዛሬ ላይ የሚስተካከለውን በማስተካከል የተሻለ ነገን መገንባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ነገን የተሻለ ለማድረግም ከንትርክ መውጣት እንደሚገባ አውስተው፥ ለፍትህ እና ዴሞክራሲ መከበር ጠንክሮ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ጥቂቶቹ ከሚያዘጋጁት አጀንዳ በመውጣትና በጎ አስተሳሰብን በመተግበር፥ ፍትህ፣ ሰብዓዊ መብት፣ ጠንካራ የስራ ባህል፣ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ እና ዴሞክራሲን ማሳካት እንደሚቻልም አስረድተዋል።

ፍትህና ዴሞክራሲም በፍላጎት ሳይሆን ለእነዚህ የሚሆን ተቋማትን በመገንባት ብቻ እንደሚመጡ ጠቅሰው፥ ከፍላጎት ባለፈ ተግባር ስለሚያስፈልግ በመደመሩ መርህ ተግቶ መስራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

አሁን ላይም ፍትህና ዴሞክራሲና ሊሸከሙና ሂደቱን ሊያፋጥኑ የሚችሉ ተቋማት ግንባታ እና፥ ለዚሁ ዓላማ ተቋማትን በመገንባት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ ባለሙያዎች ምደባ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ምርጫ ቦርድ እና የፍትህ ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ እንዲሆኑ ማሻሻያና እርምጃዎች እንደሚወሰዱም ነው የተናገሩት።

በቅርቡም በፍትህ ዘርፉ ላይ ተከታታይ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም አውስተዋል።

የፀጥታ አካላትም በህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ስራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ ማሻሻያ እየተደረገ ሲሆን፥ መከላከያ ሰራዊቱም ዘመናዊ፣ ስልጡን፣ ኢትዮጵያን የሚወክልና ከተለያዩ ጥቃቶች መከላከል በሚያስችለው ደረጃ እንዲገኝ ከጎረቤት ሃገራት ጋር በጥምረት እየተሰራ ነው።

የትምህርቱ ዘርፍም ጥራት ያለውና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ በሚመለከታቸው አካላት ውይይት እየተደረገበት መሆኑንም በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

የተጀመረው የለውጥ ሂደት እንዲፋጠንም ስራ ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን ማስተካከል፣ ግጭቶችን ማስቆምና የተሻለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በመገንባት መንግስት የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሰራም ቃል ገብተዋል።

በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም የሃገራቸው አምባሳደሮች በመሆናቸው፥ በሁሉ ዘርፍ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በሚደረገው ሃገራዊ የግንባታ ሂደትም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በቀን 1 ዶላር በማዋጣት ሃላፊነታቸውን ይወጡ ዘንድም ጠይቀዋል።

የፍራንክፈርት ከተማ ምክትል ከንቲባ ኡዌቤከር በበኩላቸው፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በሃገሪቱ በርካታ ማሻሻያዎች ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባው ማሻሻያዎቹ ተስፋ ሰጭና የሃገሪቱን የወደፊት ጉዞ ብሩህ የሚያደርጉ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም እንዲሰፍን ያደረጉትን ጥረትም አድንቀዋል፤ ከዚህ ባለፈም አዲስ በመሰረቱት መንግስት ውስጥ የተከተሉት የካቢኔ አወቃቀር ለአፍሪካ ምሳሌ ሊሆን የሚችል መሆኑንም ገልጸዋል።

ለህዝባቸው የሰጡት ተስፋና ያሳዩት አመራርም ባለፉት ሶስት አስርት አመታት በሃገሪቱ ያልታየ መሆኑንም በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

 

 

 

You might also like
Comments
Loading...