Fana: At a Speed of Life!

ለኦነግ አመራሮች የሚደረገው አቀባበል ሰላማዊ እንዲሆን በበቂ ሁኔታ ዝግጅት ተደርጓል – የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በነገው ዕለት አዲስ አበባ ለሚገቡት የአሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሮች የሚካሄደው የአቀባበል ስነ ስርዓት ሰላማዊ እንዲሆን ፓሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
 
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በሰጡት መግለጫ፥ የከተማዋ ፓሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በጋር የአቀባበል ስነ ስርዓቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
 
ባለፉት ቀናት በባንዲራና ስም ግጭት ለመቀስቀስ እንደተሞከረና በዚህም አስፈለላጊው እርምጃ እንደተወሰደ ገልፀዋል።
 
በከተማዋ የተለየ ዓላማ በማንገብ ግጭት ሲቀሰቅሱ የነበሩ አካላት በጥፋታቸው መሰረት በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።
 
ስለታማ ነገሮች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ ከአቀባበል ኮሚቴው ጋር የተሰራ ቢሆንም የተወሰኑ ሰዎች ስለተማ ነገሮችን ይዘው እንደተገኙና ፓሊስም በፍተኛ ሁኔታ እነዚህን ነገሮች መቆጣጠሩን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
 
በመሆኑም ከአሁን በኋላም ስለታም ነገሮችን ህዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ ይዞ መሄድ እንዳማይቻልና ፓሊስም አስፈላጊው ቁጥጥር ያደርጋል ተብሏል።
 
በነገው ዕለት በሚደረገው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሮች አቀባበል ስነ ስርዓት ላይ ደጋፈዎች የሚይዙትን አርማ ማክበር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
 
የከተማዋ ነዋሪዎችም ችግር ለመፍጠር የሚመክሩ አካላትና ልጆቻቸውን መከታተልና መቆጣጠር እንደሚገባቸው ምክትል ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
 
እንዲሁም አቀባበሉን ምክንያት በማድረግ ግጭት ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላት ካሉ ህብረተሰቡ ጥቆማ መስጠት አለበት ብለዋል።
 
ምክትል ኮሚሽነሩ የተለያዩ ብሄሮች እና ብሄረሰቦች መኖሪያ፣ የአለም አቀፍ ተቋማትና የዲፕሎማቶች መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ግጭት ለመፍጠር መሞከር ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
 
በኤፍሬም ምትኩ
You might also like
Comments
Loading...