Fana: At a Speed of Life!

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ዳቮስ ገቡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ስዊዘርላንድ ዳቮስ ገብተዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው ከፍተኛ የመንግሥት ልዑካን በለንደን የብሪታንያ አፍሪካ ኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ የነበራቸውን ተሳትፎ አጠናቆ ነው ወደ ስዊዘርላንድ ዳቮስ ያቀናው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ፈጣን ለውጥ እና ዕድገት ለማረጋገጥ ለአህጉሪቱ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ በፎረሙ ላይ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ዕድገት ማዕቀፍ ውስጥ በፈረንጆቹ 2025 በዋናነት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያጎለብት ፕላትፎርም መቋቋሙ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች እና ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ሃላፊዎች በጋራ ውይይት አድርገዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአህጉሪቱ ፈጣን ዕድገት በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት መረባረብ እንደሚገባ አውስተዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በየዓመቱ የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው መንግሥት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ የአፍሪካ የዕድገት ፕላትፎርም ከተቀመጠለት የጊዜ ወሰን አኳያ ሃገራት ስኬታማ ልምዶችን እና ውጤታማ ተሞክሮዎችን የሚጋሩበት መድረክ ሊፈጠር ይገባልም ነው ያሉት።

የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአፍሪካ ምዕራፍ በፈረንጆቹ 2020 መስከረም ወር ላይ አዲስ አበባ እንደሚካሄድ ጠቅሰው፥ ፎረሙ ለተሻለ ልምድ ልውውጥ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ማለታቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተያያዘም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ፕሬዚዳንት ቦርግ ብሬንደ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ በሚመክረውና በመጭው መስከረም ወር በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአፍሪካ ምዕራፍ እየተደረገ ባለው ዝግጅት ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

የፎረሙ በኢትዮጵያ መካሄድ ዓለም አቀፍ የቢዝነስና ፖለቲካ መሪዎች ጋር ለመገናኘት የማይተካ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

በስዊዘርላንድ ዳቮስ በሚካሄደው ዓመታዊው ዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ትናንት የተጀመረ ሲሆን፥ እስከ ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ቀጥሎ ይካሄዳል።

በመድረኩ ላይ የተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፥ በዓለም አቀፍ፣ በቀጠናዊ እና በኢንዱስትሪ አጀንዳዎች ዙሪያ የሚመክሩ ይሆናል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.