Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚሰማሩ 1 ሺህ ወጣቶች ገለፃ አደረጉ

ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚሰማሩ 1 ሺህ ወጣቶች በዛሬው ዕለት ገለጻ አድርገዋል።

የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከዛሬ ነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካሄድ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በዚህ ፕሮግራም ለሚሳተፉ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ገለፃ እና የስራ መመሪያ ሰጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለፃቸውም በጎ ፍቃደኛ በመሆን ህብረተሰቡን ልታገለግሉ ስትንቀሳቀሱ ለማስተማር እና ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ለማወቅም፣ ለመማርም፣ ለመቀበልም መሆን አለበት ብለዋል።

ምክንያቱም ህብረተሰቡ ውስጥ በርካታ እውቀቶችን እና ልምዶችን እንደሚያገኙ በምሳሌ በማስደገፍ ለወጣቶቹ አብራርተዋል።

በመሆኑም ወጣቶቹ በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ተግባርን ብቻ ሳይሆን መሳቅን፣ ማቀፍን እና አብሮ መብላትን እንደ መርህ ይዘው እንዲቀሳቀሱ እና የሚሄዱበትን አካባቢ ባህል እና ወግ ሊያከብሩ እንደሚገባ ዶክተር አብይ አሳስበዋል።

ዛሬ የተጀመረው በጎ ነገር እንደቀላል እንደማይታይ የገለፁት ዶክተር አብይ፥ በቀጣይም ይህ መልካም ነገር ባህል ሆኖ እንዲቀጥል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

በዚህ በጎ ተግባር የሚሰማሩ ወጣቶችን ለማበረታታትና ድርጊቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ወደ ስራ በሚሰማሩበት ወቅት እንደ እንድ መመዘኛ እንዲያዝ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

በመጨረሻም ለስምንት ሴቶችና ለሁለት ወንዶች በድምሩ ለ10 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ወደ ቻይና በመሄድ ልምድ እና ስልጠና እንዲያገኙ ፍቃድ ሰጠዋል።

በዛሬ ይፋ በተደረገው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ላይ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 1 ሺህ ተመራቂ ወጣቶች ተሳታፊዎች ናቸው።

ወጣቶቹ ከሚኖሩበት ክልል ባለፈ ወደ ሌሎች ክልሎች በመሄድ በተለያዩ ተግባራት ላይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ።

ይህ ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መካሄድ ሀገራዊ ስሜትንና የህዝብ ለህዝብ ማህበራዊ ትስስርን ያጎለብታል ተብሎ ይጠበቃል።

የበጐ ፈቃድ አገልግሎት ዜጐች በተለይም ወጣቶች ያለማንም አስገዳጅነት ለሚኖሩበት ማህበረሰብ ልማትና ለአካባቢ ደህንነት የራሳቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ነው።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፕሮግራሙን በጋራ ያስተባብሩታል።

ከወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጐ ፈቃድ አገልግሎት ባለፈ በዘንድሮው የወጣቶች የክረምት ወራት የበጐ ፈቃድ አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ 13 ነጥብ 6 ሚሊየን የሚሆኑ ወጣቶች የበጐ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

You might also like
Comments
Loading...