Fana: At a Speed of Life!

አዴኃን ወደ ሃገር ቤት ገብቶ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ ተስማማ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 10፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ /አዴኃን/ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡

በክልሉ መንግስትና በአዴኃን መካከል ሁለተኛው ምዕራፍ የድርድር ውይይት ዛሬ በአስመራ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በውይይቱም ከንቅናቄው ከፍተኛ አመራሮች ጋር አንድ ቀን የፈጀ ውይይት ማድረጋቸውንና የአማራን ህዝብ ጥቅም እንዲሁም አንድነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ ሰፊ ጊዜ ወስደው መምከራቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይም አብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን ነው ይፋ ያደረጉት፡፡

ይሁን እንጂ ተጨማሪ ድርድሮችን የሚጠይቁ አንዳንድ ነጥቦች መኖራቸውን ጠቅሰው ልዩነቶችን በማቻቻል የክልሉን ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡

ወደፊት በጋራ በሚሰሯቸው ስራዎች ላይም አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ለእርቅና ለሰላም እንዲሁም የዜጎች ነጻ ሃሳብ እንዲከበርና ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር በር መክፈቱን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ  አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናግረዋል

የተለያየ ሃሳብና አቋም ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገራቸው ገብተው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርጉ መንግስት አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያድርግ በመናገር የአስመራ ተልእኮም የዚህ አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ለውጡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሃገራት ጭምር መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን አንስተዋል፡፡

የአማራ ክልልን ጨምሮ በብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች በርካታ ኤርትራውያን በመኖራቸው ወደፊት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል፡፡

የኤርትራ መንግስት ይህንን የውይይት መድረክ በአስመራ እንዲደረግ ላደረገው ቀና ትብብርም የአማራ ክልልን በመወከል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የአዴኃን ሊቀመንበር ተፈሪ ካሳሁን ንቅናቄው ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራትና ወደ ሃገር ቤት ገብቶ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሱን ነው የገለጹት፡፡

ይሁን እንጂ ስምምነቱ የአማራ ጥያቄዎች ተመልሰዋል ብለን የተስማማነው ሳይሆን የክልል የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች እስኪመለሱ ድረስ ከብአዴን ጋር ሆነን በጋራ ለመታገል የተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በውይይት መክፈቻው ላይ የተገኙት የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ኢብራሒም ዑስማን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶር. ዐብይ አህመድ እና በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መካከል የተጀመረው የሰላም ስምምነት 38 ቀናት ማስቆጠሩን አስታውሰው ስምምነቱ የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች ፍላጎትና ስሜት በሚያረካ መልኩ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግስትና የአዴኃን አመራሮች የጀመሩት የድርድር ውይይትም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግስትና አዴኃን ወደ ውይይት መምጣታቸው የሚመሰገን ነው ያሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ ውይይቱ የሁለት ወንድማማቾች ቀና ፍላጎት የታየበት መሆኑን አድንቀዋል፡፡

በዚህ ውይይት ላይም የኤርትራ ድርሻ እንደ አደራዳሪነት ሳይሆን እንደ መድረክ አመቻችነት ሊታይ ይገባል ነው ያሉት፡፡

አቶ ንጉሱ እንዳሉት በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ንቅናቄው ይህንን ተገንዝቦ ወደ ሃገር ውስጥ በመግባት ሰላማዊ ትግል እንዲያደርግ ለተጨማሪ ውይይት አስመራ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

 

ምንጭ፦ የአማራ መገናኛ ብዙሃን

 

You might also like
Comments
Loading...