Fana: At a Speed of Life!

ከወጪ ንግዱ 2 ነጥብ 83 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2010 በጀት ዓመት ከሀገራዊ የወጪ ንግድ 2 ነጥብ 83 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱ የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

 

በበጀት ዓመቱ 5 ነጥብ 23 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ማሳካት የተቻለው የዕቅዱን 54 በመቶውን ነው ማሳካት የተቻለው ተብሏል፡፡

በግብርናው ዘርፍ 2 ነጥብ 17 ቢሊዮን የሜሪካን ዶላር ሲገኝ በማኒፋክቸሪንግ እና በማዕድን ዘርፉ እያንዳንዳቸው 458 ነጥብ 65 እና 122 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል፡፡

በግብርና ዘርፉ ከታቀደው 64 በመቶ፣ ማኒፋክቸሪንግ 45 በመቶ እና በማዕድን ዘርፉ ደግሞ 15 በመቶውን ብቻ ነው መሸፈን የተቻለው ተብሏል፡፡

ከባለፈው ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ከተገኘው 2 ነጥብ 91 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነጻጸርም የ71 ነጥብ 43 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይንም 2 ነጥብ 43 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

የበጀት ዓመቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የነዳጅ፣ ማዕድንና የተፈጥሮ ጋዝ እና ሌሎች ተቋማት ደጋፍና ክትትል ከሚያደርጉት ውጪ በበጀት ዓመቱ የንግድ ሚኒስቴር ድጋፍና ክትትል ከሚያደርግባቸው የግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ አፈጻጸም 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ በአፈጻጸሙ 964 ነጥብ 432 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት የተቻለ ሲሆን ይህም የእቅዱን 70 ነጥብ 9 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ተገልጿል፡፡

ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን በሚፈለገው ደረጃ መግታት አለመቻል፣ የምርት አቅርቦትና የጥራት ችግሮች መኖር፣ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ተከስቶ የነበረው የፀጥታና ያለመረጋጋት ሁኔታዎች፣ የተሻለ ገቢ የሚያስገኙ የገበያ ዕድሎችን በማፈላለግና ትስስር በመፍጠር ረገድ የተሰራው ስራ አነስተኛ መሆን፣ የግብዓትና የአቅርቦት ችግሮች እና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም መዘግየት ለሀገራዊው የወጪ ንግድ አፈጻጸም መቀነስ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ዋነኞቹ ችግሮች መሆናቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተያያዘም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2010 በጀት ዓመት በ230 ፋብሪካዎች ላይ የጥራት ቁጥጥር አድርጎ ምርታቸው ከደረጃ በታች ሆነው የተገኙ 22 ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ መውሰዱንም አስታውቋል፡፡

 

You might also like
Comments
Loading...