Fana: At a Speed of Life!

አቶ ጃዋር መሀመድና ሌሎች ባለሙያዎችን ያከተተ ቡድን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጎበኘ

አቶ ጃዋር መሀመድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃዋር መሀመድና ሌሎች ባለሙያዎችን ያከተተ ቡድን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጎበኘ።

በጉብኝቱ ወቅትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ለጎብኚዎቹ ስለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለጻ እና ማብራሪያ አድርገዋል።

አቶ ተወልደ፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካውያን ኩራት መሆኑን በመጥቀስ፤ ወደፊትም የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን በዚህ የስኬት ጉዞው ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ከሚነገረው በላይ በተግባር የሚታይ ነው ያሉት አቶ ተወልደ፥ የበረራ መዳረሻዎቹን፣ የአውሮፕላን ብዛት እና በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች ድርሻ መግዛቱን በማሳያነት አንስተዋል።

አየር መንገዱን ለስኬት ካበቁት ውስጥም ያለው የቁጥጥር ስርዓት፣ የገንዘብ አያያዙ እና የባለሙያዎች ታታሪነት ተጠቃሽ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ከሀገር ውስጥ የበረራ ተደራሽነት ጋር በተያያዘም ሁሉንም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እይተደረገ መሆኑንም ነው አቶ ተወልደ ያነሱት።

በቀጣይም የዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ቁጥር ለማሳደግ እና የሌሎች አየር መንገዶችን ድርሻ በመግዛት እቅዱን ለማሳካት እንደሚሰራም ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃዋር መሀመድ፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጣይ ስኬታማ እንዲሁን የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አስታውቀዋል።

የጉብኝት ቡድኑ አባል የሆኑት ፕሮፌሰር እስቄል ገቢሳም፥ አየር መንገዱ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን በአይኔ በማየቴ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብን ላመሰግን እወዳለሁ ነው ያሉት ፕሮፌሰር እስቄል።

በመሃመድ አሊ

You might also like
Comments
Loading...