Fana: At a Speed of Life!

አቶ ተስፋዬ ዑርጌ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ድጋፍ በማድረግ እጃቸው እንዳለበት መርማሪ ፖሊስ ገለጸ

አቶ ተስፋዬ ዑርጌ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 9 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በብሄራዊ መረጃና ደህንነት መምሪያ አዛዥ ናቸው ተብለው በሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት በመምራትና በማስተባበር ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፌደራል ፖሊስ ምርመራ ላይ የሚገኙት አቶ ተስፋዬ ዑርጌ በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከተከሰተው ግጭት የጦር መሳሪያና የገንዘብ ድጋፍ ጋር በተያያዘ እጃቸው እንዳለበት መርማሪ ፖሊስ ገለጸ።

የፌደራሉ የመጀመሪያ ተረኛ 1ኛ የወንጀል ችሎት መርማሪ ፖሊስ ያከናወናቸውን ስራዎች አድምጧል።

በዚህም መርማሪ ፖሊስ በአዲስ አበባ እና በክልል የሚገኙ ተባባሪ ተጠርጣሪዎችን መያዣ የማውጣት፣ የምስክር ቃል የመቀበል እና ሌሎች ስራዎች ማከናወኑን ገልጿል።

ከዚህ ባለፈም ከሰኔ 16ቱ ጥቃት ጋር በተያያዘ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር የሚገኙና እጃቸው አለበት የተባሉ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከሃገራቱ ጋር እየተወያየ መሆኑንም ጠቅሷል።

የቀሪ ምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች ላይ ከተጠርጣሪው ጋር ግንኙነትና እጃቸው አለበት የተባሉ ተጠርጣሪዎችን የማጣራት ስራ እና ሌሎች ቀሪ ስራዎችን ለማከናወንም 14 ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው በቅድሚያ ተጠርጣሪውን የማረሚያ ቤት ልብስ በማልበስ በምስል አስደግፈው የሚለቁና የግለሰቡን ስም እየጠቀሱ ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ የሚያቀርቡ የሚዲያ አካላት እንዲያስተካክሉ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ ብለዋል።

በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት አላቸው ያላቸውን አካላት አጠናቅቄያለሁ እያለና አቃቢ ህግ ክስ ለመመስረት ጊዜ እየጠየቀ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊጠይቅ አይገባም በማለትም ተቃውመዋል።

ከዚህ ባለፈም መርማሪ ፖሊስ የምርመራ ስራውን በፍጥነት እየሰራ አይደለም በማለት ፍርድ ቤቱ ከፍትህ ገጽታ አኳያ ሊያየው እንደሚገባም ተቀውሟቸውን አሰምተዋል።

ከዚህ ባለፈም ተጠርጣሪ የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው ምርመራው ቢቀጥል የሚፈጥረው ችግር የለም በማለትም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርም ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስም ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጡ የምርመራ ሂደቱን በማደናቀፍ ማስረጃ ሊያሸሹ ይችላሉ በማለት ዋስትናውን ተቃውሟል።

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤትም ማንኛውም ሚዲያ የሁለቱን ወገን ጉዳይ በሚዛናዊነት እንዲያቀርብ በማለትና ዋስትናውን በማለፍ ለፖሊስ ተጨማሪ 8 ቀን ሰጥቷል።

 

 

በታሪክ አዱኛ

Comments
Loading...