Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አነሳ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በሃገሪቱ ተጥሎ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አነሳ፡፡

ምክር ቤቱ በስብሰባው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ በ63 ተቃውሞ በ21 ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ እንዲነሳ ወስኗል፡፡

ይህን ውሳኔ ተከትሎ÷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ያላጠናቀቃቸው ጅምር ስራዎች ካሉ ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት ከዛሬ ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንዲያደርግ ተወስኗል፡፡

በተመሳሳይ የፍትህ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ የጀመሯቸውን ጉዳዮች በመደበኛው የፍትህ አሰሰጣጥ ስርአት እንዲያጠናቅቁም ነው የተወሰነው፡፡

ሕውሃት እና ግብረአበሮቹ በሃገሪቱ ህልውና እና ሉአላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ የደቀኑ በመሆኑ እና ይህን አደጋ በመደበኛው የህግ ማስከበር ስራ መከላከል የማይቻል ሆኖ በመገኘቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014ን ያወጀ ሲሆን፥ ይህ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በአዋጅ ቁጥር 1264/2014 ፀድቆ በስራ ላይ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥር 18 ቀን 2014 ዓመተ ምህረት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማውጣት የግድ አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎ የነበረው ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑ እና ስጋቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ስራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን በመጠቆም ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈፃሚነት ጊዜ እንዲያጥር በመወሰን የውሳኔ ሀሳቡ እንዲፀድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን ተከትሎ ነው ዛሬ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ በመወያየት አዋጁን ያነሳው፡፡

በሃይለየሱስ ስዩም

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.