Fana: At a Speed of Life!

እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሰ አካል ጉዳተኛ ህፃናት መካከል 92 በመቶ የሚሆኑት የትምህርት እድል እንዳላገኙ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሰ የአካል ጉዳተኛ ህፃናት መካከል 92 በመቶ የሚሆኑት የትምህርት እድል አላገኙም ተባለ።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ደርጅት የአካል ጉዳተኞች ስምምነትን ከተቀበሉ ሀገራት አንዷ ብትሆንም በአካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዳልተሰራ መረጃዎች ያመለክታሉ።

እስከ 2008 ያለው የትምህርት ሚኒሰቴር መረጃ እንደሚያመለክተው እድሜያቸዉ ለትምህርት ከደረሰ የአካል ጉዳተኛ ህፃናት መካከል ስምንት በመቶዉ ብቻ የትምህርት እድል እንዳገኙ ይጠቁማል።

ድህነት እና የቤተሰብ እና የህብረተሰብ የአመለካከት ችግር ለአካል ጉዳተኛ ህፃናት የትምህርት እድል አለማግኘት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።

ከዚህ ባለፈ ድህነቱን እና የአመለካካት ተጽዕኖዉን ተቋቁመው ትልቅ ደረጃ መድረስ የቻሉ ቢኖሩም የስራ እድል ያገኙት የአካል ጉዳተኞች ሁለት በመቶ ብቻ መሆናቸው ተነግሯል።

የዚህ ችግር ሰለባ ከሆኑት መካከል የ32 አመቷ አይነ ስውር ወጣት ቤዛዊት አየልኝ ትጠቀሳለች።

ቤዛዊት በቋንቋና ስነ ጽሁፍ የትምህርት ዘርፍ በዲግሪ ብትመረቅም ላለፉት ሁለት አመታት ያለስራ እንደቆየች እና ያደረገችው የስራ ፍለጋ እንዳልተሳካለት ትናገራለች።

ይህም ተቋማት በአካል ጉዳተኞች ላይ ያላቸው እምነት ዝቅተኛ እንደሆነ እንደሚያሳይ ቤዛዊት ተናግራለች ።

በመንግስት ተቋማት የሚወጡ የስራ ቅጥር ማስታወቂያዎች በብሬል እና በምልክት ቋንቋ የተደገፉ ባለመሆናቸው እንዲሁም የስራ ቅጥር ፎርሞችም አካል ጉደተኞችን ያገናዘቡ ባለመሆናቸው ፈታኝ እንደሆኑ ቤዛዊት ገልፃለች።

አካል ጉዳተኞች ሸክም ላለመሆን በብዙ ፈተና እና እልህ አስጨራሽ ትግልን አልፈው እራሳቸውን ለመቻል በሚያደርጉት ጥረት መንግስት ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስባለች።

ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲው ሆነ ስርአተ ትምህርቱ ወይም ካሪክለሙ የችግሩ መነሻ መሆናቸውን አስታውቋል።

በሚኒስቴሩ የልዩ ፍላጎት አካቶ ትምህርት ቡድን መሪ አቶ አለማየሁ ወልደ ቂርቆሰ፤ የትምህርት ካሪኩለሙ ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ሁኔታን በማገናዘብ ለአካል ጉዳተኛዉ በሚመች መልኩ መቅረፅ ቢያስፈልግም ተግባረዊ አልተደረገም ብለዋል።

እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ ለምን እና በማን እንደተወሰነ ሳይታወቅ በሀገሪቱ የአይነስውራን የሂሳብ ትምህርት እስከ 6ኛ ክፍል ብቻ እንዲማሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በትምህርት ስልጠናና ፖሊሲው ላይ በየደረጃው ለሚገኙ የትምህርት ክፍሎች ለስልጠና የሚመለመሉ እጩ መምህራን ችሎታ፣ ታታሪነት፣ እንዳግባቡ የአካል ብቃታቸዉ፣ የአዕምሮ ጤንነታቸዉ እና ለሙያው ያላቸዉ ዝንባሌ በመስፈርትነት ሰፍረዋል።

በዚህም በ2003 በወጣዉ የመምህራን ምልመላ መመሪያ ከአንደኛ እስከ ስምተኛ ክፍል መስማት የተሳናቸው መምህራን እንዳያስተምሩ እንዲሁም ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ደግሞ አይነስውር መምህራን እንዳያስተምሩ እንደሚከለክል ተነግሯል።

ሆኖም በሀገሪቱ የትምህርት ህግ ባለመኖሩ የአካል ጉዳተኞች ስለመብታቸው የሚጠይቁበት እድል እንደሌለ ነው አቶ አለማየሁ የገለፁት።

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ተቋማት ፍላጎትን መሰረት አድርገዉ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት አካቶ ትምህርትን ለመጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለዚህም መመሪያ እና ስትራቴጅ የተቀረፀ ሲሆን፥ ከፊንላንድ መንግስት ጋር በመተባበር በክልሎች የድጋፍ መስጫ ማዕከላት እንደተቋቋሙ ነው ተብሏል።

በመምህራን በኩል ያለዉን የብቃት ችግር ለመቅረፍም በስምንት ዩንቨርስቲዎች እና በ18 የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች የልዩ ፍላጎት መምህራን ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ ፖሊሲው ላይ ያሉ ገዳቢ ሀሳቦች እንዲሻሻሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የአካል ጉዳተኛውን መብት ጥሰት ለመቀነሰ ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን በብዛት ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።

የሚኒስቴሩ የማህበራዊ ደህንነት ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ ጀምበር፤ ስለአካል ጉዳት የሚጠይቁ የስራ ቅጠር ፎርሞች በስራ ስምሪት አዋጁ የተከለከለ እና የሚያስቀጣ እነደሆነ ገልፀዋል።

የአለም ባንክ እና የአለም የጤና ድርጅት በ2011 ያወጡት መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ 17 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል አካል ጉዳተኛ እነደሆነ ይጠቁማል።

የዘርፉ ባለሙያዎችም ሀገሪቱ የአካል ጉዳተኞችን ጥቅም ለማስከበር እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካል ጉዳተኞች ስምምነት በተጨማሪ ፕሮቶኮሉን ልትፈርም እና የትምህርት ህግም ሊኖራት እንደሚገባ ያስታወቁት።

በቤተልሄም ጥጋቡ

You might also like
Comments
Loading...