Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ቴሌኮም ደንበኞች ቁጥር 66 ነጥብ 2 ሚሊየን ደርሷል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ጥቂት አመታት በቴሌኮም ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች ሀገሪቱን አለም አቀፍ መመዘኛን ያሟላ የዘርፉ ኩባንያ ባለቤት እንዳደረጋት ኢትዮ ቴሌኮም ይገልጻል።

በሚጥለው አመት 125 አመት የሚሞላው የኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ ብዙ መልኮችን አልፎ ዛሬ ላይ ደርሷል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አንዱአለም አድማሴ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የሃገሪቱ የቴሌኮም ዘርፉ ከ12 አመት በፊት በዝግመቱ እንደሚታወቅ ያነሳሉ፤ ከዚያ ወዲህ ባሉት አመታት መሻሻል ማሳየቱን በመጥቀስ።

መንግስትም ከእነዚህ አመታት ወዲህ የቴሌኮም ዘርፉን ለማሻሻል የተለያዩ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶችን እንዳደረገም ተናግረዋል።

ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ለቴሌኮም ማስፋፊያ ብዙ በሚባል ደረጃ በፈረንጆቹ 2006 1 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተደርጓል።

በወቅቱ የተንቀሳቃሽ ስልክ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለና የመደበኛ ስልክ ፍላጎት ከፍ እያለ መምጣቱ ለዚህ ምክንያት እንደነበር ይነገራል።

በዚህም አቅርቦቱ እያደገ ከመጣው ፍላጎት አንጻር በቂ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የቴሌኮም ኢንዱስትሪውን የተሻለ ስምና አቅም ባለው ኩባንያ መምራት በማስፈለጉ፥ የ30 ሚሊየን ዩሮ ፕሮጀክት ተጠይቆ መተግበሩን ዋና ስራ አስፈጻሚው ያስታውሳሉ።

በወቅቱም የወጣውን ጨረታ የፈረንሳይ ኩባንያ በማሸነፍ የኮንትራት ማኔጅመንት መውሰዱን ጠቅሰው፥ ዘርፉ ለሁለት አመት ተኩል በኩባንያው ከተዳደረ በኋላ ሀገሪቱ አለም አቀፍ ደረጃ ያለው የቴሌኮም ኩባንያ ባለቤት መሆኗንም ነው የተናገሩት።

ኩባንያውም የተቋሙን አስተዳደር፣ ስርጭት፣ ማርኬቲንግና ሽያጭ እንዲሁም ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ በማዘመን የኔትወርክ አቅምን ሙሉ ለሙሉ ለደንበኞች ለማስተላለፍ መስራቱንም አንስተዋል።

ይሁን እንጅ ያለውን አቅም አሟጦ ከመጠቀም አንጻር አቅርቦቱ ተጠቃሚው በሚፈልገው ደረጃ ያለመድረስ ችግር መከሰቱንም አስታውሰዋል።

በዚህ ሳቢያም 13 የቴሌኮም ሰርክሎች የተቀረጹበት እና 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ወጪ የተደረገበት፥ የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት ማካሄድ አስፈልጓል ነው ያሉት።

በተሰራው ስራም ሃገሪቱ አሁን ላይ ከ80 ሚሊየን በላይ የተንቀሳቃሽ ስልክ ደንበኞችን የሚያስተናግድ ኔትወርክ ባለቤት መሆኗን አስረድተዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም አሁን ላይ 66 ነጥብ 2 ሚሊየን ደንበኞች ሲኖሩት፥ በበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራትም 27 ነጥብ 79 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ይሁን እንጅ ኩባንያው የገቢውን ያህል የአገልግሎት ጥራት የለውም የሚል ትችት ይቀርብበታል፤ ተቋሙ በበኩሉ ከመሰረተ ልማት ስርቆት ጀምሮ የተለያዩ ችግሮችን በማንሳት ለሚቀርብበት ትችት ምክንያት መሆናቸውን ይገልጻል።

በሌላ በኩል የኩባንያው ትርፋማነት በተጋነነ የአገልግሎት ታሪፍ ላይ የተመሰረተ እንደሆነም ተጠቃሚዎቹ ያነሳሉ።

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ በበኩላቸው ኩባንያው በታሪፍ ጉዳይ ላይ የሚቀርቡ ትችቶችን በሙሉ አይቀበልም ባይ ናቸው።

ለዚህም በመደበኛ የስልክ አገልግሎት በአለም ዝቅተኛ ክፍያ እንሚያስከፍል ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ ከተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ግን በድምጽ አገልግሎት ብቻ እንደሚወዳደር አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን ከሞባይል ዳታ ክፍያ ጋር ተያይዞ ከምስራቅ አፍሪካም ሆነ ከሌሎች ሃገራት አንጻር ታይቶ የሚስተካከልበት ሁኔታ ይኖራል ብለዋል።

ኩባንያው በደንበኞች ብዛትም ሆነ በገቢ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከእርስ በርስ ግንኙነቶች ባለፈ፥ ለኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ፋይዳ ያላቸው ጅምር እንቅስቃሴዎች መታየታቸውንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ይገልጻሉ።

ከዚህ አንጻርም በግብርናውና ጤናው ዘርፍ መረጃ ማግኘት የሚያስችሉ የፅሁፍ መልዕክት አገልግሎቶች መሰጠታቸውንም ለአብነት ያነሳሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ላይ በስፋት ሊሰራ ይገባል ነው የሚሉት።

አሁን ኢትዮ-ቴሌኮም ያለው አቅም እና የደንበኞቹ ቁጥር ከመቀራረቡ አንጻርም ሶስተኛ ዙር የማስፋፊያ ስራ ውስጥ ለመግባት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው።

ይህም ከ100 ሚሊየን በላይ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎችን በደንበኝነት ማቀፍ የሚያስችል ነው ተብሏል።

አሁን በኢንተርኔት እስከ 4ጂ ያሉ ጅማሬዎች ያሉ ስራዎች የዘርፉ ያለፉት አመታት የስኬት ማሳያ ሲሆኑ፥ የአገልግሎት ጥራትና መሰል ጉድለቶች ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮችእ ናቸው።

በካሳዬ ወልዴ

You might also like
Comments
Loading...