Fana: At a Speed of Life!

ለንግድ ፍቃድና ምዝገባ የሚደረገውን ምልልስ ለማስቀረት እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለንግድ ፍቃድና ምዝገባ ምልልስ የሚደረግባቸውን ተቋማት በመረጃ መረብ በማስተሳሰር የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳለው አገልግሎቱ የንግድ ፍቃድና ምዝገባ አገልግሎት ፈላጊዎችን እንግልት ያስቀራል ተብሎ ታምኖበታል።

የንግድ ፍቃድ አውጭዎች ፍቃዱን ለማግኘት መረጃዎችን ለማሟላት ከገቢዎች ጀምሮ የተለያዩ ተቋማት መመላለሳቸው ቅሬታን ሲያስነሳ ቆይቷል ።

ቢሮ ከ3 ዓመታት በፊት ይህን ችግር ለመፍታት አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ቅሬታዎችን መፍታት ቢችልም፤ ሆኖም ግን አሁንም ድረስ ከተገልጋዮች የሚነሱ ቅሬታዎች አልታጡም ።

ከቅሬታዎቹ መካከልም ከብቃት ማረጋገጥ፣ የመለያ ቁጥር ምዝገባ እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ከቢሮ ወደ ሌላ ተቋማት የሚያደርጉት ምልልስ እና የቀጠሮ ብዛት ጊዜ የሚወስድ እና ምቹ አለመሆኑን ተጠቃሽ ነው።

ቢሮውም የተገልጋዮች መጉላላት እንዳለ አምኖ፤ ችግሩ የሚመነጨዉ በዋነኝነት ቢሮ ለብቻው ለንግድ ምዝገባ እና ፍቃድ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን የማይሰጥ በመሆኑ ነው ይላል።

በቢሮ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማይ ሶሎሞን፥ ከቢሮ ጋር የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚሰራዉ ስራ በኔትወርክ ያልተሳሰረ በመሆኑ ስራው በተገልጋዮች ምልልስ የሚከወን በመሆኑን ያስረዳሉ።

ይህን ከግምት በማስገባት ብቃት አረጋጋጭ ተቋማትን ጨምሮ ከገቢዎች ጋር በሰርቨር በማስተሳሰር የአንድ መስኮት ሊጠናቀቅ የሚያስችል ስርአት ለመዘርጋት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ እንደሚሉትም ከቢሮው ጋር የሚሰሩ 132 ጣቢያዎችን በማስተሳሰር ስራ የተጀመረ ሲሆን፥ እስከ ሰኔ ድረስም በሙከራ ደረጃ ከአራት ባለድርሻ ተቋማት ጋር የማስተሳሰር ስራው ይጠናቀቃል።

የሶፍትዌር ግንባታ ሂደቱም በመፋጠን ላይ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በመጪዉ ሀምሌ ወር ምልልስ የሚበዛባቸዉን፤ አራት ተቋማት በመለየት በመረጃ መረብ በመስተሳስር ስራው ይጀመራል።

ከዚህ 429 የዘርፍ ልየታ በማድረግ ከዚህ ቀደም ከሁለት እና ከዛ በላይ ተቋማት ይመለከተኛል የሚሏቸውን ዘርፎችም ወደ አንድ ይመጣሉ ብለዋል።

በባለሙያ እጥረት፣ ፋይል ባለመሟላት እና ሌሎች ችግሮችንም እንዲሁ ይፈታል በተባለው በዚህ አሰራር ከተገልጋዮች እንግልት በተጨማሪ ህገ ወጥ አሰራሮችንም ሊከላከል የሚችል መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ የሚገልጹት።

በአጠቃላይም ለዚህ የአንድ መስኮት አገልግሎት ፕሮጀክት ከ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ዌጪ ይደረግበታል ተብሏል።

በሀይለሚካኤል አበበ

You might also like
Comments
Loading...