Fana: At a Speed of Life!

ፋና ቴሌቪዥን የፊታችን ቅዳሜ ይመረቃል

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፋና የቴሌቪዥን የፊታችን ቅዳሜ ጥር 26 2010 ዓ.ም ይመረቃል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብሩክ ከበደ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ፋና የቴሌቪዥን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በተገኙበት ይመረቃል ብለዋል።

የፊታችን ቅዳሜ የሚካሄደው ፋና የቴሌቪዥን ምርቃት የአዲስ ስራ የሽግግር ምእራፍ ማብሰሪያ መሆኑንም አቶ ብሩክ ተናግረዋል።።

በቀጣዮቹ ጊዜያትም በሂደት የሚጀምሩና የሚታደሱ ተመልካቾቹን ተሳታፊና ባለቤት የሚያደርጉ መርሃ ግብሮችን ይዞ ፋና ቲቪ በአዲስ ምእራፍ ይቀጥላል ብለዋል።

ፋና ህዝብ በይፋ የሚወያይበት፣ የሚናገርበት፣ የሚሳተፍበት የተለያዩ መድረኮች እና እና ዝግጅቶች አሉት ያሉት አቶ ብሩክ፥ እነዚህ መድረኮች በቴሌቪዥን ጣቢያውም ይቀጥላሉ ብለዋል።

እንዲሁም በይፋ ውይይት የሚደረግባቸው መድረኮችም እንደሚኖሩ የገለጹ ሲሆን፥ ቀጣዩ ምእራፍ እነዚህም ወደ አየር የሚበቁበት ጎዜ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ፋና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በጥልቀት የሚፈተሹበት፣ የመንግስት ሃላፊዎች ቀርበው የህዝቡን ጥያቄዎች የሚመልሱበት፣ የሀሳብ ልዩነቶች የሚታዩበትና የሀሳብ ፉክክር የሚንጸባረቅበት ጣቢያ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።

የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶችን ያካተተው ፋና ቴሌቪዥን የህብረተሰቡን ባህልና እሴቶች የጠበቁና ህብረተሰቡን ያከበሩ የመዝናኛ ዝግጅቶችንም ይዞ በቴሌቪዥን ሚዲያ አዲስ ምእራፍ ለመጀመርና ለውጥ ለማምጣት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ፋና ቴሌቪዥን መረጃ መስጠት ማዝናናትና ማሳወቅ ብቻም ሳይሆን ሙሉ ቤተሰብ በጋራ ሊመለከተው የሚችልና ሁሉም የሚፈልገውን የሚያገኝበት እንዲሁም ጥያቄው ምላሽ የሚያገኝበት፣ ሃሳቡ ቦታ የሚያገኝበት፣ የራሱን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ራሱንም የሚመለከትበት ጣቢያም ነው ሆኖ የሚቀጥለው።

“ነጻ አስተሳሰብ ለተሻለ ህይወት” በሚል መሪ ሃሳብ የተነሳው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፤ መሪ ሃሳቡን “በህይወት ፍጥነት” በሚል መሪ ሃሳብ አሳድጎ ለተሻለ ህይወት ነጻ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን ፍጥነት የሚያስፈልግ መሆኑንና ለውጡም ፈጣን መሆን እንዳለበት ለማሳየትና በዚህ ልክም ለመስራት የተነሳ ሚዲያ ነው።

አቶ ብሩክ፥ “በህይወት ፍጥነት ስንል አንዱ ነባራዊ እና ተጨባጭ መሆን እና ጊዜው የሚጠይቀውን ፍጥነት ማሟላት ነው” ይላሉ።

“ሁሉም ነገር ህይወት ራሷ በምትፈልገው እና ሀገር በምትፈልገው ፍጥነት እንዲሁም ህብረተሰቡ በሚፈልገው ፍጥነት አንዲራመድ የመንገር፣ የማሳሰብ እና ራስንም እዚህ ውስጥ የመክተትና በዚህ ፍጥነት የመስራት ቃል መፈፀሚያ ነው” ብለዋል።

አቶ ብሩክ እንዳሉት፥ የጣቢያውን መሪ ሃሳብ በተግባር ለመተርጎም የሚያስችል በትናንትና ማነቆ ውስጥ ያልተያዘ ዛሬ ላይ ለነገ የሚተርፍ ትርጉም ያለው ስራ ለመስራት የሚያስችልና ሰዎችንም የሚያነሳሳ ስራ ለመስራት ሙሉ ዝግጅት አድርጎ በሰው ሃይልም ሆነ በቴክኖሎጂ ብቁ ሆኖ እየሰራ ያለ ሚዲያ ነው።

“ፋና ወሳኙ ቀን ዛሬ ነው የሚል ተቋም እና ሰራተኛ ፈጥሯል” ያሉት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው “ ይህንን የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ነው የሚያስፈልገው፤ ባለን አቅም ሁሉ ይህንን የሚመጥን ኤች ዲ ቴክኖሎጂ ተጠቅመናል” ሲሉም ተናግረዋል።

ዝግጁነቱ ታዲያ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር አብረው በሚሰሩ ተባባሪ አዘጋጆችም ይገለጻል፤ ተባባሪ አዘጋጆቹና ዝግጅቶቹ በልዩ ጥንቃቄ የተመረጡ መሆናቸውንም አቶ ብሩክ በመግለጫቸው ላይ ጠቁመዋል።

ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀው የፋና ቴሌቪዥን ጣቢያና ስቱዱዮም የኢፌድሬ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ ተባበሪ አዘጋጆችና የፋና ቤተሰቦች በተገኙበት የፊታችን ቅዳሜ በይፋ ይመረቃል።

የፋና ቴሌቪዥን ስርጭት ከ6 ወራት በፊት ሙከራ የጀመረ ሲሆን፥ ከታህሳስ 2 2010 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የፕሮግራም ስርጭት በመጀመር የህዝቡን ፍላጎት ማሟላት ጀምሯል።

 

በትእግስት ስለሺ

You might also like
Comments
Loading...