Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከ30 ሀገራት መሪዎች ጋር ውይይቶችን አካሂዳለች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 24፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በ30ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ከ30 ሀገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቷን የሚያሳድጉ ውይይቶችን ማካሄዷን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ቃል አቀባዩ ባለፈው ሰኞ በተጠናቀቀው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮዽያ ከፍተኛ ወጪ ሳታወጣ በርካታ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ያከናወነችበት ነው ብለዋል።

ከመሪዎች ስብሰባ ጎን ለጎን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፥ ከ30 ሀገራት መሪዎች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ብሄራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ዙርያ ተወያይተዋል።

አዲስ አበባ በዚህ ስብሰባ 10 ሺህ ተሳታፊዎችን ያስተናገደች ሲሆን፥ 678 ጋዜጠኞችም ከመላው አለም ስብሰባውን ለመዘገብ መታደማቸውን አቶ መለስ ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ተሰሚነቷን ያሳደገችበት የገፅታ ግንባታዋን በስፋት ያስተዋወቀችበት እና በርካታ ተሳታፊዎች በመምጣታቸው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያገኘችበት ነው ብለዋል።

ናይጀሪያ፣ ጋና እና አንጎላን የመሰሉ ሀገራት የራሳችን አየር መንገድ እንዲኖረን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በጋራ እንስራ የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውንም ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አንስተዋል።

በተያያዘ ዜና ኢትዮጵያ አፍሪካዊያንን በማስተሳሰር አብነት የሆነችበትን የዲፕሎማሲ ስራ አጠናክራ መቀጠል አለባት ሲሉ የቀድሞው የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ሩፒያህ ብዉዛኒ ባንዳ ገልፀዋል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ይህን ያሉት ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ጋባዥነት በፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ነው።

ሩፒያህ ብዉዛኒ ባንዳ ኢትዮጵያ ከንጉሰ ነገስቱ ዘመን ጀምሮ ለአፍሪካዊያን አንድነት የምታደርገው እንቅስቃሴ የነፃነት አብሪ ኮከብ ያደርጋታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ፓን አፍሪካኒዝም እንዲስፋፋ እና በርካታ ሀገራት ከቅኝ ገዥዎች ቀንበር እንዲወጡ ለማድረግ የከፈለችው ዋጋ በቀላሉ የሚገመት አይደለም ነው ያሉት።

You might also like
Comments
Loading...