የሲዳማና የኦሮሞ ህዝብን ለማጋጨት መታገል ለድካም ይዳርግ እንደሆን እንጂ አይሳካም -አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ
አዲስ አበባ፣ግንቦት 23፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የሲዳማና የኦሮሞን ህዝብ ለማጋጨት መታገል ለድካም ይዳርግ እንደሆን እንጂ አይሳካም ሲሉ የሲዳማ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ ተናገሩ፡፡
የኦሮሞና የሲዳማ ህዝብ የሰላም ኮንፈረንስ በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በኮንፈረንሱ ንግግር ያደረጉት የሲዳማ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ የሲዳማና የኦሮሞ ህዝብ አንድነት አሁን የተጀመረ ሳይሆን በተፈጥሮ የታደለ አብሮ በመኖር እሴት የተገመደ ነው ብለዋል፡፡
ድንበር ባሉ ወረዳዎች የሚከሰተው ግጭት የተፈጥሮ የፍላጎት አለመግባባት እንጂ የሁለቱን ህዝብ ተቃርኖ የሚያሳይ አለመሆኑንም አመላክተዋል።
ሲዳማና ኦሮሞ 90 በመቶ ድንበር ይጋራሉ ያሉት አቶ አለማየሁ ይህ ህዝብ እርስ በራሱ ተጋጭቶ አያውቅም፤ ነገር ግን ችግሮች በድንበር ሁልጊዜም ይከሰታሉና የሚከሰቱ ችግሮችን በበሰለ አይን ማየት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የምዕራብ አርሲ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሀጂ በበኩላቸው የግጭቶቹ መንስኤ ድንበር መገፋፋትና የግጦሽና ሌሎችም የግለሰቦች ግጭቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በትግሉ ወቅት አብሮ ትልቅ ዋጋን የከፈለ፣ ተፈጥሮ ያስተሳሰረውና ተለያይቶ መኖር የማይችለው የኦሮሞና የሲዳማ ህዝብ በምንም ምክንያት የከረረ ግጭት ውስጥ አይገባም በመሆኑም የሚፈጠሩ ትናንሽ ችግሮችን ቀድሞ ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ሀይሌ ጉርሜሳ በድንበር አካባቢ በተደጋጋሚ ግጭቶች ተከስተው እንደነበር አስታውሰው፥ በሀገር ሽማግሌዎች የዳበረ ግጭት የመፍታት ልምድ በእርቅ መፈታታቸውን ገልፀዋል፡፡
በቅርብም የተከሰተው ግጭት ከዚህ የበለጠ ባለመሆኑ በእርቅ መፈታት የሚችል መሆኑን ነው የተናገሩት።
ነገር ግን በድንበር አካባቢ የሚከሰቱ ችግሮችን ምክያት በማድረግ ሁለቱን ህዝብ ለማራራቅ የሚሰሩ አካላት እንዳሉ ማህበረሰቡ በመገንዘብ፥ የሚያጋጩ ነገሮች ሲከሰቱ በዳበረው የእርቅ ስነስርዓት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በቅርቡ በሲዳማና ምዕራብ አርሲ ወረዳዎች መካከል የተከሰተው ችግር አሁን ላይ መፈታቱን እና ችግሩን ያባባሱ አካላትም በህግ እየተጠየቁ መሆናቸው ተመላክቷል።
በጥላሁን ይልማ