Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ በዶክተር ደብረጽዮን የክስ መዝገብ የተካተቱ ተከሳሾች በመገናኛ ብዙሃን እንዲጠሩ ትእዛዝ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የክስ መዝገብ የተካተቱ ተከሳሾች በጋዜጣና በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ጥሪ እንዲደረግላቸው ትእዛዝ ሰጠ።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ በትግራይ ክልል ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን ጨምሮ በመዝገቡ የተካተቱት 37 ተከሳሾችን አፈላልጎ ማቅረብ እንዳልቻለ ለፍርድ ቤት ገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ ተከሳሾቹ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ  ለማድረግ የጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግ ይፈቀድልኝ ሲል አቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ-ሽብርና ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ተከሳሾች በጋዜጣና በኢቢሲ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በችሎቱ በዚሁ መዝገብ ሥር የተካተቱት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ዶክተር አዲስዓለም ባሌማ፣ ዶክተር አብርሃም ተከስተን ጨምሮ 17 ተከሳሾች በችሎቱ ተገኝተው ጉዳያቸውን ተከታትለዋል።

ፍርድ ቤቱ ፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ላልዋሉት ተከሳሾች መጥሪያ እንዲያደርስ በተደጋጋሚ ትእዛዝ የሰጠ ቢሆንም ፖሊስ በክልሉ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ትእዛዙን መፈፀም አልቻልኩም በማለት ቀርቦ ለችሎቱ አስረድቷል።

ችሎቱ በወንጀለኛ መቅጫ 162/1 መሠረት በቁጥጥር ሥር ያልዋሉትን 37 ተከሳሾች በጋዜጣና በኢቢሲ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዛዝ ሰጥቷል።

ችሎቱ የተፈቀደውን የጋዜጣና የቴሌቪዥን ጥሪ ምላሽ ለመጠባበቅ ለግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.