Fana: At a Speed of Life!

ያልተጠናቀቁ የካፒታል ፕሮጀክቶች በ2015 በጀት ዓመት በአነስተኛ ወጪ ለአገልግሎት እንዲበቁ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል – ዶክተር እዮብ ተካልኝ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 በጀት ዓመት አዳዲስ ካፒታል ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደማይደረጉ እና ያልተጠናቀቁ የካፒታል ፕሮጀክቶችን በአነስተኛ ወጪ በትጋት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ገለጹ፡፡

የ2015 በጀት አመት የፌዴራል መንግስት በጀት ባነሰ ወጪ ብዙ ስራ ለማከናወን በሚያስችል ጥብቅ የፊሲካል ፖሊሲ ማዕቀፍ በመመራት እየተዘጋጀ መሆኑንም የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታው ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር የፖሊሲ ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ የ2015 በጀት አመት የበጀት ዝግጅትን አስመለክተው እንደገለጹት ÷170 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ከገንዘብ ሚኒስቴር በተሰጣቸው የበጀት ጣሪያ መሰረት ከሚያዚያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የ2015 በጀታቸውን ለሚኒስቴሩ አቅርበው ማስገምገማቸውን ጠቅሰዋል ፡፡

የ2015 በጀት በጥብቅ የፊሲካል ፖሊሲ ማእቀፍና የሀገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑን መናገራቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የበጀት ዝግጅቱ ስትራቴጂያዊ ለሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ማለትም ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለማዕድን፣ ለቱሪዝምና ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን ዶክተር እዮብ አመልክተው፥ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ ደግሞ ከመደበኛ በጀት ላይ እስከ 40 በመቶ የሚሆን ቅናሽ እንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡

የበጀት ጉድለትን በተመለከተም ከውጭ የሚገኘው ሀብት በታሰበው መጠን ላይገኝ ስለሚችል መንግስት ከሀገር ውስጥ ከሚመነጨው ሀብት ማለትም ከግምጃ ቤት ሰነድና ከሌሎች የሀገር ውስጥ ምንጮች ለሟሟላት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ነድፎ ተግባራዊ በማድረጉ አበረታች ውጤት በመገኘቱ የበጀት ጉድለቱ የዋጋ ግሽበትን በማያባበስ ሁኔታ ለማሟለት ጥረት ይደረጋልም ብለዋል፡፡

በ2015 በጀት አመት አዳዲስ ካፒታል ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደማይደረጉ ዶክተር እዮብ ጠቅሰው ይልቅ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የካፒታል ፕሮጀክቶች በአነስተኛ ወጪ በትጋት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት እንዲቻል የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የ2015 በጀታቸውን ባስገመገሙበት ወቅት ጥብቅ መመሪያ እንደተሰጣቸውም አስረድተዋል፡፡

የ2015 የፌዴራል መንግስቱ በጀት ለህዝብ ተወካዮች ምክር በቤት ቀርቦና ውይይትና ክርክር ተደርጎበት ሲጸድቅ ከሀምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ እንደሚውል ይታወቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.