Fana: At a Speed of Life!

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የጥንቃቄ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው – የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንዳንድ የዓለምና የአፍረካ አገራት የተከሰተውን የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ለመከላከል የሚያስችሉ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

“መንኪ ፖክስ” የተሰኘውና በቫይረስ የሚከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው በምዕራብ አፍሪካ ሲሆን ፥ አሁን ላይ በሽታው ከ50 ዓመት በኋላ በምዕራቡ ዓለም ዳግም ብቅ ብሏል።

በሽታው በሰውነት ላይ የመቁሰል አደጋ የሚያስከትል ሲሆን ፥ በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች ወይም ከእንሰሳት ጋር በሚኖር ንክኪ ሊተላላፍና ሊዛመት እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።

እስካሁን ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድስ፣ ጣሊያን፣ ስዊትዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ካናዳ፣ አሜሪካና አውስትራሊያ ቫይረሱ የተገኘባቸው አገራት የሚቀሱ ሲሆኑ ፥ በእነዚህ አገራት በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ወደ መቶ እንደሚደርስ ተገልጿል።
በሽታው አፍሪካ ውስጥም መግባቱ የተዘገበ ሲሆን ፥ ለአብነትም ሞሮኮ በዛሬው ዕለት 3 የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምልክት የታየባቸው ሰዎች ማግኘቷን አስታውቃለች።

ይህንንም ተከትሎ በኢትዮጵያ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለኢዜአ የገለጸው።

በኢንስቲትዩቱ የቅድመ ማስጠንቀቅና የመረጃ ሥርዓት አስተዳደር ዳይሬክተር ዘውዱ አሰፋ ፥ ኢትዮጵያ የበሽታውን ሥጋት ለመቀነስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።

በተለይም ኅብረተሰቡን ስለቫይረሱ በማስተማር በሽታውን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መጀመራቸውን ነው የገለጹት።

በዚህም ዜጎች ወደተለያዩ አገራት ጉዞ ሲያደርጉ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለተጓዦችና ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቫይረሱ ቢከሰት እንኳን በቀላሉ ለመቆጣጠር ለትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችና ተጠቃሚዎች ለሕክምና ባለሙያዎችም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ጎን ለጎንም አገሪቱን ከሌሎች አገራት ጋር በሚያገናኙ ድንበሮች ላይ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ የቅኝት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው አቶ ዘውዱ የተናገሩት።

በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ሙቀት፣ ራስ ምታት፣ የጀርባና የጡንቻ ሕመም፣ የሰውነት አልፎ አልፎ ማበጥና መቁሰል፣ በማንኛውም ነገር ላይ ፍላጎት ማጣት ይታይባቸዋል።

ሕመሙ በራሱ ጊዜ የመጥፋት ባህሪም ያለው ሲሆን ፥ ከ14 እስከ 21 ቀናት እንደሚወሰድበትም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኅብረተሰቡ የበሽታውን ምልክቶች በሚያይበት ጊዜ በቅርቡ ላለው ጤና ተቋም እንዲሁም በነፃ የስልክ መስመር በ8335 እንዲያሳውቅም ኢንስትቲዩቱ አሳስቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.