Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለፋሲካ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለፋሲካ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው ሰዎች በዓሉን ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍና ማዕድ በማጋራት ወገናዊ ኀላፊነታቸውን በመወጣት ሊሆን እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።

“ትንሣኤ ክርስቶስ ለሙታን ሁሉ በኵር ሆኖ የተነሳበት እንዲሁም የነጻነት፣ የትዕግስት፣ የጽናት፣ የመስዋእትነት፣ የይቅርታ፣ የመተሳሰብና የመደጋገፍ ተምሳሌት ነው” ብለዋል በመልዕክታቸው።

የክልሉ መንግሥት በጦርነት እና በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን በዓሉን በአብሮነትና በደስታ እንዲያሳልፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብትዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳም በዓሉን በማስመልከት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከትንሳዔ በዓል የላቀ ፍቅርን፣አክብሮትን ዝቅ በማለት የላቀ ከፍታ እንዳለ የምንረዳበት ነው ሲሉም ጠቁመዋል።

በዓሉን ስናከብር በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመርዳት እና በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው እንደገለጹት፥ በበዓላት ወቅት የመደጋገፍና የመረዳዳት የቆየ ባህላችንን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በተለይ አቅመ ደካማ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ ፣በማይመች ሁኔታ ላይ ሆነው በዓልን የሚያሳልፉ ወገኖቻችንን አለንላችሁ ልንላቸው ይግባልም ነው ያሉት።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾም የፋሲካ በዓልን በማስመልከት ባስተላፉት መልዕክት “በዓሉ ስለሰው ልጆች ፍቅር በመስቀል ላይ በተከፈለ ዋጋ የተገኘ” መሆኑን አስታውሰዋል።

ሲከበርም ማኅበራዊ አንድነትን በማጠናከር፣ በመዋደድና በመከባበር እንዲሁም፥ ለአረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ፍቅርና ክብር በማሳየት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው÷ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለፋሲካ በዓል አደረሳችሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ህዝበ ክርስቲያኑ በፆም ወቅት ያሳየውን መልካም ተግባር በበዓሉ ወቅትም በማጎልበት የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት እና ህሙማንን በመጠየቅ ወገናዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ህዝቡ ለዘመናት የቆየውን የማካፈል እና የመረዳዳት ባሕል ሳይለቅ አሁንም ለተቸገሩ ወገኖቹ ካለው እንዲያካፍል ጠይቀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ያለንበት ሁኔታ ፈተናና ተስፋ የተቀላቀለበት በመሆኑ ህዝቡ ዛሬ በገጠመው ችግር ተስፋ ሳይቆርጥ በታሪክ የመረዳዳት ባሕሉንና ያለውን የማካፈል ከጥንት ጀምሮ የዘለቀ ልማዱን እንዲቀጥልበትም ርዕሰ-መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሰ-መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ÷ የኢየሱስ ክርስቶስን አስተምህሮት፣ ስቅለት እና ትንሳኤ እንዲሁም ለሰው ልጆች መድህን ለመሆን የተቀበለውን ፍዳ በመልዕክታቸው አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ላለፉት ሁለት ወራት በጾም ጸሎት ለሀገር ሰላም እና በረከት በመለመን እንዲሁም የክርስትና አስተምህሮ በሚያዘው መሰረት መልካም ነገሮችን በመፈጸም ለቆዩ እና በነገው እለት የትንሳኤ በዓልን ለሚያከብሩ የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ ሲሉ በዓሉ የሰላምና የፍቅር እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

በዓሉ ሲከበር የእምነቱ አስተምህሮ በሚያዘው መሰረትና በተለመደው ኢትዮጵያዊ የመደጋገፍ ባህልና እሴት መሰረት በተለያየ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖችን አስበን ያለንን በማካፈል፣ማእዳችንን በማጋራትና መልካም በማደረግ ሊሆን ይገባልም ብለዋል፡፡

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።ትንሳኤው ፍቅር ጥላቻን፤ እውነት ሃሰትን፤ ደግነት ክፋትን ያሸነፉበት በዓል ነው ብለዋል።

በአሉ ሰላም፣ ፍቅር፣ አብሮነት፣ ተስፋ ፣ ይቅርታ የሚያብብበት መተሳሰብ የሚጎላበት ያዘኑ የሚፅናኑበት፤ ካለን የምናካፍልበት፤ የታረዙት የሚለብሱበት፤ ማዕዳችንን የምናጋራበት ይሁንልን ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጆሀር ባስተላለፉት መልዕክት ትንሣኤ ለሰው ልጆች ሁሉ ከመከራ የመነሳት የተስፋ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ በመኾኑ እኛም አሁን የገጠሙንን የውስጥና የውጭ ችግሮች ተቋቁመን ፈተናዎችን በፅናት ለመሻገር መነሳት ይኖርብናል ብለዋል።

ፍቅርንና አንድነትን በመስበክ ማክበር ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራኒዮ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ዘላለማዊ የሞት መጋረጃን ከማስወገዱም ባሻገር በምድር ላለን ፍቅርን፣ ትህትናን፣ መልካምነትንና ለሌሎች ስንል መስዋዕትነት መክፈልን አስተምሮናል ብለዋል በመልዕክታቸው።

መላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ምንም የሌላቸውን ወገኖችን በመርዳት፤ ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያን በመደገፍ ያላው ለሌለው በማካፈል በዓሉን ማክበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.