Fana: At a Speed of Life!

የእስራኤል ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ለመሰማራት መዘጋጀታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ለመሰማራት ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታወቁ፡፡
 
በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ÷በአገሪቱ ባለሃብቶች የተመሰረተውና በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ከተሰማራው የ”10 ግሪን ጊጋዋት ለኢትዮጵያ” የተባለው ኩባንያ አመራር አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይታቸውም ድርጅቱ በኢትዮጵያ በፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ያቀረበውን አዲስ የኢንቨስትመንት ሀሳብ በሚመለከት ምክክር አድርገዋል።
 
የኩባንያው ተወካዮች ባደረጉት ገለፃ፥ ባለሃብቶቹ በኢትዮጵያ የሶላር ኃይል ኩባንያ ለመክፈት ያላቸውን እቅድ በዝርዝር አቅርበዋል።
 
አምባሳደር ረታ ኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ኃይል ሃብት እንዳላት እና የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል በመግለጽ÷ በአገሪቱ ያለውን የውጭ ኢንቨስትመንት የሕግ ማዕቀፍ አብራርተዋል፡፡
 
“ኢትዮጵያ የ13 ወር የፀሐይ ብርሃን ጸጋ ያላት አገር ተብላ የምትታወቅ በመሆኑ፣ ከፀሃይ ታዳሽ ኃይል ማምረት አገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልማት ግቦቿን እንድታሳድግ ይረዳታል” ሲሉ በዘርፉ ያሉትን እድሎች አስረድተዋል።
 
የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚካኤል ዓለሙ በበኩላቸው÷ ኩባንያው ለግብርና፣ ለጤና፣ ለቱሪዝም እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ከ50 ኪሎ ዋት እስከ 5 ሜጋ ዋት የሚደርሱ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችል አስረድተዋል።
 
ኩባንያው በሀገር ውስጥ የኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ተቋም በመመስረት የሶላር ፓናል የመገጣጠም፣ በአገር ውስጥ ያለውን እጥረት በዘርፉ ሙያዊ አቅም ለማጠናከር ማቀዱንም ነው ያስታወቁት።
 
የኩባንያው ተወካዮች በቀጣይ በኢትዮጵያ የሥራ ጉበኝት እንደሚያደርጉ መግለጻቸውንና÷ ሁለቱ ወገኖች ይህ እቅድ እንዲሳካ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.