Fana: At a Speed of Life!

የኢንቨስትመንት ባንኮችና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የመዋዕለ ነዋዮች ሰነድ ገበያ ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን እየገለጹ ነው -የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንቨስትመንት ባንኮችና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የመዋዕለ ነዋዮች ሰነድ ገበያ ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን እየገለጹ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።
 
የካፒታል ገበያን በኢትዮጵያ ለመጀመርና ገበያውን ለመምራት የጸደቀውን አዋጅ በማስመልከት ማብራሪያ የሰጡት በባንኩ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ መለሰ ምናለ÷ የአዋጁ መጽደቅ የገበያው ተዋንያን፣ የቁጥጥር ስርዓቱን፣ በገበያው ላይ ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን ለመቆጣጣር የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
 
የካፒታል ገበያ አዋጁ መፅደቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉን የመምራት ሃላፊነት ስላለበት የፕሮጀክት ቡድን አቋቁሞ ለካፒታል ገበያው እውን መሆን የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ አንዱ መሳሪያ እንደሆነ ገልጸዋል።
 
በአዋጁ ትርጓሜ መሰረት የመዋዕለ ነዋይ ሰነድ ገበያ ማለት የሰነዶች ሽያጭ፣ ግዥ፣ ልውውጥ፣ የሽያጭ ዋጋ፣ እንዲሁም ክፍያ በቋሚነት የሚፈፀምበት ቦታ መሆኑን እንደሚያብራራ ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ የጀመረችው የሰነደ የመዋዕለ ነዋይ ገበያ በሌሎች አገሮች ካለውና በተለምዶ የስቶክ ወይም የአክሲዮን ገበያ ከሚባለው ጋር ተመሳሳይ አለመሆኑን አስረድተዋል።
 
ሆኖም ኢትዮጵያን ጨምሮ የተወሰኑ ሀገራት የስቶክ ገበያን የስያሜ ለውጥ በማድረግ (Securities Exchange) በሚል መጠቀም መጀመራቸውን በማንሳት የስያሜ ለውጡ የተደረገውም ስቶክ ገበያ ከአክሲዮን ግብይት ጋር ብቻ በመያያዙና አሁን ብዙ መዋዕለ ነዋይ ሰነዶች በመምጣታቸው ነው ብለዋል።
 
ለአብነትም በሰነደ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ ሊሸጡና ሊገዙ የሚችሉት ከአክሲዮኖች በተጨማሪ፣ የባለ እዳነት ሰነዶች፣ ብድሮች፣ ቦንዶች፣ ወደ ካፒታልነት ሊቀየሩ የሚችሉ ሰነዶች፣ በመንግስት የወጡና ለግብይት የሚውሉ የህዝብ ብድር ሰነዶች፣ ከመዋዕለ ነዋይ ጋር የተያያዙ ውሎች፣ የኢንቨስትመንት ፈንድ የድርሻ ሰነድ ይገኙበታል ነው ያሉት።
 
በካፒታል ገበያ አዋጁ መሰረት ቼክ፣ የተስፋ ሰነድ፣ የሃዋላ ወረቀት፣ የንግድ ወረቀቶችን፣ ሌተር ኦፍ ክሬዲት፣ ጥሬ ገንዘብ ማስተላለፍና በባንኮች መካከል የሚተላለፉ ሰነዶች፣ የመድን ፖሊሲዎች፣ ለተጠቃሚዎች ከጡረታ ክፍያዎች የሚመነጩ መብቶች በመዋዕ ንዋይ ሰነድነት አይካተቱም።
 
ኢትዮጵያ በካፒታል ገበያ አዋጁ መሰረት የመዋዕለ ነዋዮች ሰነድ ገበያን ለመጀመር በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗን የሰሙ የውጭ ኩባንያዎች በገበያው ለመሳተፍ እያማተሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
 
ገበያው ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት መሆኑን የጠቀሱት አማካሪው÷በዚህም አዋጁ በፀደቀበት ሰሞን በዓለም ታዋቂ የሆኑ ሶስት የሰነድ ገበያ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን በማሳየታቸው የቴክኒክ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
 
ኩባንያዎቹ የቴክኖሎጂ አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም በባለድርሻነት ለገበያው የሚጠቅሙ የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት አማራጭ ማቅረባቸውን አንስተው÷ የቴክኖሎጂ አቅርቦቱን ይዘው በገበያው ባለድርሻነት ለሚሳተፉት በራችን ክፍት ነው ብለዋል።
 
በቅርቡ የመዋዕለ ነዋዮች ሰነድ ገበያን ለመጀመር ፕሮጀክት መቋቋሙን ተከትሎ የውጭ ባለሃብት የሆነው ኤፍ ኤስዲ አፍሪካ ባለድርሻ ለመሆን በኢንቨስትመንት መሳተፍ መጀመሩን ገልጸዋል።
 
ከኤፍ ኤስዲ አፍሪካ ባሻገርም ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽንን (አይ ኤፍ ሲ) በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋዩን ለማፍሰስ ፍላጎት ማሳየቱን እና የኤፍ ኤስዲ እና የአይ ኤፍ ሲ በኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ ነዋይ ገበያ መሳተፍም ሌሎች ኩባንያዎች እንዲመጡ የሚያነሳሳ መሆኑንም ተናግረዋል።
የካፒታል ገበያ ተቆጣጣሪ ባለስልጣኑ በይፋ ፈቃድ መስጠት እስከሚጀምር ተዘጋጅተው እየጠበቁ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ኢትዮጵያ በምትጀምረው የሰነድ ገበያ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች የእውቀት ሽግግር እንደሚያፋጥኑም ጠቁመዋል።
 
ከሰነድ ገበያ ኩባንያዎች ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ትላልቅ ልምድ ያላቸው የኢንቨስትመንት ባንኮች፣ የሽያጭ ዋጋ ተመን አውጭዎች፣ ገበያ አከናዋኞችና የቢዝነስ አማካሪዎችም ፍላጎታቸውን እያሳዩ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

ለተጨማሪ መረጃ ቪዲዮውን ይመልከቱ፡-

 

 
በመሆኑም የሰነድ ገበያውን የሚያቋቁመው የፕሮጀክት ቡድን ቴክኖሎጂ፣ እውቀትና ካፒታል ይዘው እንዲመጡ የገበያውን አጠቃላይ የቢዝነስ እቅድ በፍጥነት ያከናውናል ያሉት አማካሪው÷በዚህም በሰነደ መዋዕለ ነዋዮች ገበያ ወደ ኋላ የቀረችውን ኢትዮጵያ ወደፊት ለማሻገር እንሰራለን ብለዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.