Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ህዝብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ከተመልካችነት ወደ እውነተኛ የመወሰኛ ጠረጴዛ ላይ መጥቷል – የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ህዝብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ከተመልካችነት ወደ እውነተኛ የፖለቲካ መወሰኛ ጠረጴዛ ላይ መጥቷል ሲል የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገለጸ፡፡
በክልሉ የተካሄዱ ህዝባዊ ውይይቶችን፣ ድርቅንና የመስክ ጉብኝቶችን አስመልክቶ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው÷በሶማሌ ክልል የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የህዝብንና እንስሳትን ህይወት ለመታደግ የክልሉ መንግሥት በሠራው ጠንካራ ስራ ድርቁ ያስከተለውን ችግር መቋቋም እንደተቻለ ተመላክቷል፡፡
ድርቁን በመቋቋም ረገድ የተለያዩ ክልሎች፣ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ባለሀብቶች፣ ለጋሽና ግብረሰናይ ድርጅቶች እንዲሁም መንግሥት ላደረጉት ድጋፍና ትብብር ክልሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡
በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ መዝነብ በመጀመሩ የድርቁ አደጋ መቀነሱን የጠቆመው መግለጫው÷ ድርቁን ለመቋቋም እንደተደረገው ርብርብ ሁሉ በድህረ ድርቁ ጊዜም የክልሉ መንግሥት ዝግጅት አድርጎ ወደ ስራ መገባቱን ገልጿል፡፡
በክልሉ የበልግ ዝናብ መዝነብ በመጀመሩ ከዝናብ በድርቁ የተጎዱ ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም በዝናቡ ምክንያት በወንዞችና ተፋሰስ አካባቢዎች ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ አደጋዎች፣ ወረርሽኝና ተዛማጅ ጉዳዮችን ለመከላከል ጠንካራ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸው ተመላክቷል፡፡
የክልሉ አደጋ ስጋት አመራርና የጤና ቢሮ አመራሮች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ወደ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በመውረድ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንዲሰጡ ክልሉ ኮሚቴዎችን አዋቅሮ ማሰማራቱም ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የሶማሌ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎች አስመልክቶ ከህዝቡ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች፣ በሰላም፣ በልማት፣ በኑሮ ውድነት፣ በድርቁ ሁኔታና መፍትሔዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል።
በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ እንዲሁም በፌዴራል መንግሥት የተገኙ ውክልናዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ከተመልካችነት ወደ እውነተኛ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ የሶማሌ ህዝብ መሻገሩን ያሳያል ብሏል መግለጫው፡፡
የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የመንገድና የውሃ ፕሮጀክቶች ከድርቁ በኋላ እንዲሰሩ ህዝቡ ጥሪ አቅርቧል።
የክልሉ መንግሥት በሁሉም ዘርፍ በሕዝቡ የተነሱ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችንና ሀሳቦችን እንደ ግብዓት እንደሚወስድ እና ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሰጥም ነው ያሳወቀው፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.