የምስራቅ ጎጃም ዞን በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት ለደረሰበት የሰሜን ወሎ አስተዳደር ከ15 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ ጎጃም ዞን በአሸባሪው ወራሪ ቡድን ጉዳት ለደረሰበት የሰሜን ወሎ አስተዳደር ከ15 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አድርጓል፡፡
የምስራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የህልውና ዘመቻው ሎጀስቲክ አስተባባሪ አቶ መንበሩ ዘውዴ፥ የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ከዞኑ ነዋሪዎች ያሰባሰበውን ሐብት በአማራ ክልል ከባድ ወድመት ከደረሰባቸው ዞኖች መካከል አንዱ ለሆነው የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር 5 ሺህ 749 ኩንታል ምግብና ምግብ ነክ እህል ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፉ በገንዘብ ሲተመንም ከ15 ሚሊየን 227 ሺህ 401 ብር በላይ እንደሚሆን ነው የተመለከተው፡፡
ድጋፉ የእለት ደራሽ ምግብን ጨምሮ አልባሳት እና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡ በህልውና ዘመቻው ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች ይከፋፈላልም ነው የተባለው፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋው ባታብል፥ የምስራቅ ጎጃም ዞን ህዝብ ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ህዝቡ ለወገን ደራሽነቱን በተግባር አረጋግጧል ብለዋል፡፡
የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር የህልውና ዘመቻው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በተከታታይ ለ8 ዙር ግንባር ላይ ተሰማርቶ ለነበረው የፀጥታ ሀይልና በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለወገን ደራሽነቱን በተግባር አረጋግጧል።
ዞኑ እስካሁን ባለው ግዜም የዛሬውን ድጋፍ ሳይጨምር በአይነት ከ750 ሚሊየን ብር የሚገመት የአይነትና ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ የጥሬ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በጎንደር ከተማ የሚገኘው የጠዳ ጤና ሣይንስ ኮሌጅም በአሸባሪው ኃይል ዘረፋና ሙድመት ለደረሰበት ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ 320 ሺህ ብር የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ምናለ አየነው በመረጃው ጠቁሟል
፡፡