ኤጀንሲው የዲጂታል ኢኮኖሚውን ከጥቃት በሚጠብቅ መልኩ ለአምስት አመት የዘረጋውን የትራንስፎርሜሽን ስራ መተግበር መጀመሩን አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ከጥቃት በሚጠብቅ መልኩ ለአምስት አመት የዘረጋውን የትራንስፎርሜሽን ስራዎች መተግበር መጀመሩን አስታወቀ፡፡
ተቋሙ ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ የራሱን የትኩረት አቅጣጫ በማስቀመጥ እንደ ሃገር የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት የሚያስችለው ቁመና ላይ የሚያደርስ ትራንስፎርሜሽን ስራዎችን መተግበሩን ገልጿል፡፡
ከዚህ ቀደም ተቋሙ የነበረውን የተደበላለቀ የሃላፊነት ሚና በማስተካከል በተልዕኮ ላይ ብቻ ለመስራት መወሰኑንም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ይግዛው ገልጸዋል፡፡
በሃገሪቱ የተጀመረውን ትላልቅ የመሰረተ ልማት ግንባታ መሰረት ያደረጉ የበይነ መረብ ጥቃቶች በርከት ብለው መስተዋላቸውንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
ኤጀንሲው ጥቃቶቹን በጥሩ ሁኔታ መመከቱንና ከዚህ በኋላም ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚሰነዘሩ የመረጃ መረብ ጥቃቶችን ጊዜው በሚጠይቀው አቅም ለመመከት ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በተለይም ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ዛቻዎችና የተሰነዘሩ ጥቃቶችን መመከቱን ጠቅሰው በቀጣይም መሰል ጥቃቶችን ለማክሸፍ ዝግጁ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የበይነ መረብ ጥቃት የመከላከል ስራውን እንደከዚህ ቀደሙ ብቻውን ሳይሆን ሌሎች አካላትን ባሳተፈ መልኩና ድጋፍ በማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የተቋሙን ተልዕኮና አላማ የሚያሳይ አዲስ ሎጎ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡
ሎጎው በዲጅታል ኢኮኖሚው ውስጥ ለሚሰነዘሩ ጥቃቶች ጋሻነትን፤ መጠበቅ፣ መከላከልና ግድ ሲሆንም ማጥቃትን የሚገልጽ እንዲሁም አርቆ አሳቢነትን የሚያሳይ ተደርጎ መዘጋጀቱንም አውስተዋል፡፡
የኤጀንሲው ዝግጁነት እንዳለ ሆኖ ቴክኖሎጅ አጠቃቀም ላይ ማህበረሰቡም ሆነ ተቋማት በሃላፊነት እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ ተቋማት የቴክኖሎጅ ደህንነት ጥበቃ ትክክለኛ መለያ መያዛቸውን እርግጠኛ ከሆኑ ጥቃቶችን ለማክሸፍ ቀላል መሆኑንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
በፍሬህይወት ሰፊው