Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከአንዳንድ ሀገራት ተጋርጦባት የነበረውን ከፍተኛ ጫና ማለፍ የቻለችው በአፍሪካውያን እገዛ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ እና አንዳንድ ሀገራት ተጋርጦባት የነበረውን ከፍተኛ ጫና ማለፍ የቻለችው በአፍሪካዊያን እገዛ መሆኑን አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ከሚካሄደው የአፍራካ ህብረት የመሪዎች የአካል ስብሰባ ቀደም ብሎ የሚካሄደው የአባል ሃገራቱ 40ኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትናንትናው እለት መጀመሩ ይታወሳል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጉባኤውን ለመታደም ለተገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የዲኘሎማቲክ ማህበረብ አባላት በትናትናው እለትም ምሽቱን የእራት ግብዣ አድርገዋል።

በስነ-ስርአቱ ላይ አቶ ደመቀ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና አንዳንድ ሀገራት ተጋርጦባት የነበረውን ከፍተኛ ጫና ማለፍ የቻለችው በአፍሪካዊያን እገዛ ነው ብለዋል።

አቶ ደመቀ የተቀናጀውን የአንዳንድ አለምአቀፍ ተቋማት እና ሀገራት ፀረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ በአፍሪካውያን ወንድማዊ ድጋፍ ማሸነፍ መቻሉን የገለፁ ሲሆን፥ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተጠርቶ የነበረው የጄኔቫው ጉባኤ የዚህ ማሳያ መሆኑን አንስተው፤ ልዩ ጉባኤው የአንድም አፍሪካ ሀገርን ድጋፍ እንዳላገኘ በንግግራቸው በመግለፅ የአፍሪካዊያን ምን ያህል ከኢትዮጵያ ግን እንደቆሙ አሳይተዋል ነው ያሉት።

አቶ ደመቀ በንግግራቸው ኢትዮጵያዊያን በድምፃቸው መንግስታቸውን መምረጣቸውን አስታውሰው፥ ይህ በህዝብ የተመረጠው መንግስት ከቀደሙት በተለየ በካቢኔው ውስጥ ተቃዋሚዎችን ማቀፉን ጠቅሰዋል።

ሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለማስፈን ተከታታይ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑንና በቅርቡ በእስር ላይ የነበሩ ሰዎችን መፍታቷን አንስተዋል።

በተግዳሮቶችም ውስጥ ሆና ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማረጋገጥ እየጣረች እንደምትገኝ ያመለከቱ ሲሆን፥ ለዚህም የታላቁ የኢትዮጵያ ህደሴ ግድብን እንደ አንድ ማሳያ ጠቅሰዋል።

ተለዋዋጭ በሆነው አለም አቀፍ ጉዳዮች አፍሪካ ተገቢ ስፍራ እንዲኖራት ብዙ መሰራት እንደሚገባ የጠቀሱት አቶ ደመቀ፥ ለዚህም ስኬት ኢትዮጵያ አብዝታ እንደምትሰራ አስገንዝበዋል።

የተባበረች እና የበለፀገች አፍሪካ እውን እንድትሆን ሁሉም የህብረቱ አባል ሀገር እንዲተባበር አቶ ደመቀ ጨምረው በንግግራቸው ጥሪ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.