Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ህልውናዋ እና ሉዓላዊነቷ አደጋ በተጋረጠበት ጊዜ ሁሉ ችግሮቿን ለመጋፈጥ ፖሊስ ግንባር ቀደም ተሰላፊ ነበር – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ህልውናዋ እና ሉዓላዊነቷ አደጋ በተጋረጠበት ጊዜ ሁሉ ፖሊስ ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የፖሊስ አመራርና አባላት የምስጋናና የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላም ጊዜ በየሰፈሩ በጦርነት ጊዜ በየግንባሩ ሰላም ለማስጠበቅ ደፋ ቀና የሚለው የፌደራል ፖሊስ ከብዙ ድል በኋል ክብረ በአሉን ለማክበር እና ተቋማዊ ስራውን ለህዝብ ለማሳየት በቅቷል ብለዋል፡፡

“ለዚህም እንኳን ደስ አላችሁ ልንላቸው ይገባል” ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ህልውናዋ እና ሉዓላዊነቷ ለአደጋ በተጋረጠበት ጊዜ ሁሉ ፖሊስ ግንባር ቀደም ተሰላፊ ነበር ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡

ሰዎች ወደ መከራ እና ግጭት ሲገቡ የሰላምን ዋጋ ቢገነዘቡም ለእናንተ ተገቢውን ክብር እምብዛም ያልሰጠን ቢሆንም ሰላም የምናድረውና ሃገራችንን ለማበልፀግ የምንጥረው እናንተን ተማምነን ነው ብለዋል፡፡

እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ እና የሰላምና ደህንነት ተቋማት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ብልፅግና መሰረቱ ሰላም ስለሆነ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የብርሃንን ጥቅም የምናውቀው በጨለማ እንደሆነ ሁሉ የህግ አስከባሪዎችን ሚና የምናውቀው ሰላም እና ደህንነታችን አደጋ ላይ ሲወድቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ የሰላምን ዋጋ ብንገነዘብና ብናውቅ ለአፍታም ቢሆን ወደ ግጭት አናመራም ብለዋል።

በፖሊሶች የከሸፉ ወንጀሎችን ሳይሆን ከፖሊሶች እይታ ያመለጡ ወንጀሎችን አግዝፎ የመመልከት ባህል አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ፖሊስ በየዘመናቱ፣ በየወራቱ እንዲሁም በየቀኑ ለእኛ ማይነግረው ወንጀሎች ያከሽፋል፤ ነገር ግን ያከሸፈውን፣ የለፋበትን ያላመሰገንን ወንጀል ሲፈፀም ጣታችንን ልንቀስርና ልንወቅሳቸው አይገባም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በእጅጉ ለሚያገለግሏት ፖሊሶች በቂ ደሞዝ ባትከፍል እንኳ ማክበርን መለማመድ አለባትም ነው ያሉት፡፡
አላማችን ለእውነት የሚኖሩ፣ በእውቀት የሚሰሩ ፣ በስነ ምግባር የዳበሩ፣ ሙያቸውን የሚያከብሩ እና ለህዝብ የሚሰሩ ፖሊሶችን ለኢትዮጵያ ማበርከት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የጀመርነው የፀጥታ ተቋማት ሪፎርም ትልቅ ምዕራፍ የሚያደርሰን ጅማሮ ነው ሲሉም ገልፀው፡፡
አሁን የዘመነው እና የተደራጀው የፌደራል ፖሊስ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በዚህም ለመዘመኑ አስተዋፅኦ ላደረጋችሁ የፖሊስ አመራሮችና የፀጥታ አካላት የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል ብለዋል፡፡
የፖሊስ ሪፎርም ደፋር የሆኑ መልካሞችን ለማፍራት ነው ፤ ደፋርነታቸውም አላማቸውን ከግብ ለማድረስ ነው ያሉ ሲሆን፥ መልካምነታቸው ደግሞ ህዝባቸውን ለመጠበቅ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊሶች ከወንጀለኞች ጋር የሚያዋጋቸው ከፊት ለፊት የቆሙትን አሸባሪዎች፣ ወንጀለኞችን በመጥላት ሳይሆን ከኋላ የተሰለፉትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህፃናት፣ አዛውንትና አቅመ ደካሞችን የመከላከል ሃላፊነት ስላላቸው ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ በጎችን ከተኩላዎች ለመጠበቅ 24 ሰዓት የሚሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ፖሊሶች ከተኩላዎች ምስጋና እንደማይኖር አውቃችሁ በዓላማ ፅናት የኢትዮጵያን ንፁሃን ከተኩላዎች ለመታደግ አበክራችሁ ቀጥሉ ሲሉም አሳስበዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.