Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ኔዘርላድ በኢንዱስትሪ እና በግብርና ዘርፍ የሚያደርጉት ኢኮኖሚያዊ ትብብር በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል – የገንዘብ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና የኔዘርላድ መንግስታት በኢንዱስትሪ እና በግብርና ዘርፍ የሚያደርጉት ኢኮኖሚያዊ ትብብር በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከኔዘርላንድስ ኤምባሲ የተውጣጡ አመራሮች በዱከም፣ቢሾፍቱ እና ሞጆ አካባቢዎች በኔዘርላንድ ኢንቨስተሮች እየተከናወኑ ያሉ የአግሮ ኢንዱስትሪና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶችን ጎብኝተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሰመሬታ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት ፥ የኔዘርላንድ መንግስት እየሰጠ በሚገኘው የልማት ትብብር ድጋፍ፣ በኢትዮጵያ የግብርናን አቅም በማሳደግና በአግሮ ኢንዱስትሪ በተለይም በወተት ተዋጽኦና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

የኔዘርላንድ የልማት ድርጅትና ኢንቨስተሮች በአካባቢውና በመላ ኢትዮጵያ የሚያከናውኗቸው የልማት ስራዎች በተቀናጀ ሁኔታ በመመራታቸው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠራቸውም በላይ የገበያ ትስስር በመፍጠር የወተት ተዋጽኦና የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻላቸውን እና የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ቲጅስ ውድስታር የኢትዮጰያና የኔዘርላንድ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑንና ኔዘርላንድ በኢትዮጵያ 10ኛ ትልቋ ኢንቨስተር መሆኗን ጠቁመው ፥ የኔዘርላንድ የልማት ድርጅትና የኔዘርላንድ ኢንቨስተሮች በተለይ በአግሮ ኢንደስትሪ፣ በወተት ተዋጽኦና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመስክ ምልከታው በኔዘርላንድ የልማት ድርጅት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ በአቮካዶ ችግኝ ልማትና በወተት ተዋጽኦ ልማት የተሰማሩ ሴቶች የደረሱበት ደረጃ የተጎበኘ ሲሆን ፥ በሚሰሩት ስራ ውጤታማ መሆናቸውንና ኑራቸውም እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ዘርፍ ለ163 ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩንም ከሚኒስቴሩ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.