Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካን በ2030 የጦር መሳሪያ ድምፅ የማይሰማባት አህጉር የማድረግ አጀንዳ የኅብረቱን መሪዎች አወያየ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካን በ2030 የጦር መሳሪያ ድምፅ የማይሰማባት አህጉር የማድረግ አጀንዳ በኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ተነስቶ ክርክር ተደርገበት።

በኅብረቱ የፖለቲካ፣ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲባዮ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፥ በአፍሪካ እየተባባሱ የሚገኙ ኢ-ህገ መንግስታዊ የመንግስት ለውጦች፣ ጽንፈኝነት እና ሽብርተኝነትን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ደካማነት አህጉሪቱን የጦር መሳሪያ ድምፅ የማይሰማባት ለማድረግ የተያዘው አጀንዳ ገቢራዊነት መሪዎችን አከራክሯል።

የኅብረቱን አባል ሀገራት ዜጎች ደህንነት ለማረጋገጥ በአህጉር ደረጃ በአንድነና በብርታት ካልተሰራ በስተቀር አፍሪካን የጦር መሳሪያ ድምፅ የማይሰማባት አህጉር የማድረግ አጀንዳ የመሳካት እድሉ አጠራጣሪ እንደሆነም መነሳቱን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

በጉባኤው ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም የአፍሪካ መሪዎች በተለይ ኢ-ህገ መንግስታዊ የመንግስት ለውጦችን በእጅጉ ኮንነዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የትኛውንም ወታደራዊ የስልጣን ሽግግር እና መፈንቅለ መንግስት ፈጽሞ እንደማይቀበልም መሪዎቹ አረጋግጠዋል፡፡

ለዚህም በማሊ፣ ጊኒ፣ ሱዳን እና ቡርኪናፋሶ ላይ የወሰዳቸው ከኅብረቱ አባልነት እስከማገድ የደረሱ እርምጃዎችን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡

ኅብረቱ የኢትዮጵያን ጉዳይ በማንሳት ከግጭቱ መነሻ ጀምሮ ብቸኛው መፍትሄ ፖለቲካዊ አማራጭ መሆኑን አምኖ ሲሰራ እንደቆየም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

በርናባስ ተስፋዬ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.