Fana: At a Speed of Life!

አገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ጉልህ ሚና አለው – በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሚካሄደው አገራዊ ምክክር በአገሪቱ የሚስተዋሉ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ጉልህ ሚና እንዳለው በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ኪራ ስሚዝ ሲንድብጀርግ ገለጹ፡፡
አምባሳደር ኪራ ስሚዝ ሲንድብጀርግ÷ዴንማርክ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን በመቋቋም የሰላም ሂደት መጀመሩን እንደምትደግፍ ተናግረዋል፡፡
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላትን አግኝተው ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት አምባሳደሯ÷ በዚህም ኮሚሽኑ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባማከለ መልኩ አካታች ውይይት በማድረግ ግጭቶችን መፍታት የሚያስችል ጠቃሚ ስብስብ መፈጠሩን ተገንዝቤያለሁ ብለዋል፡፡
አገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም የራሳቸውን ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚችሉበት እድል በመሆኑ የኮሚሽኑ አባላት እንዳብራሩላቸውያነሱት አመባሳደሯ÷ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸው ተግባራትን ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ ከወዲሁ መግባባትን እየፈጠረ መሄድ አንደሚጠበቅበትም ነው የጠቆሙት፡፡
መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው÷ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ በርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እየገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዴንማርክ መንግስት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ያረጋገጡት፡፡
የዴንማርክ የልማት ትብብር ሚኒስትር ፍሌሚንግ ሞለር ሞርተንሰን በሶማሌ ክልል ጎዴ ድርቁ ያደረሰውን ጉዳት እንደተመለከቱ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህም ዴንማርክ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግና በዘላቂነት ኢትዮጵያን ለማገዝ እንደምትሰራ ሚኒስትሩ ማረጋገጣቸውንም ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ወደ ዴንማርክ ከተመለሱ በኋላ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች 20 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ድጋፉም በዋናነት በድርቁ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ከመደገፍ ባሻገር ችግሩን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚሰሩ ስራዎችን የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
አምባሳደሯ ዴንማርክ የተጀመረው የምክክር ሂደት እንዲጠናከር፣ የሰብዓዊ እርዳታ በበቂ እንዲደርስ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ሂደት ላይ የሚጠበቅባትን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.