Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚውን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር አቅዷል -አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚውን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ማቀዱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አስታወቁ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ከናይጄሪያ መንግስት ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል።
የናይጄሪያ የልዑካን ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ከተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልምድ ለመቅሰም እንደሆነ ተገልጿል።

በውይይቱ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚውን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር አቅዷል።

እቅዱን ለማሳካትም አራት የተቀናጁ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ለሙከራ ተግባር ተገንብተው ከመካከላቸው ሶስቱ ተመርቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ፓርኮቹን ለማዘመን ቃል መግባቱን እና የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ለአርሶ አደሩ የስራ እድልና የገበያ ትስስር ጥሩ አስተዋፅዖ እንዳላቸው ጨምረው ገልፀዋል።

የሁለቱ እህትማማች አገራት ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ከዚህ በበለጠ መሻሻል እንደሚገባው ገልጸዋል ።

ሚኒስትሩ በናይጄሪያ መንግስት የሚጠየቁትን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍን በተመለከተ ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

የልኡካን ቡድኑ መሪ እና የሀገሪቱ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ሞሀመድ ማህሙድ አቡበከር ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል የተሰማቸውን አድናቆት ገልፀው፥ አፍሪካ የተትረፈረፈ እና ያልተነካ ሃብት እንዳላት የማይካድ ነው ብለዋል።

ይህንን ጥቅም ላይ ያልዋለ ሃብት በጥሩ ሁኔታ ለመጠቀም ጠንካራ ፖሊሲ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ ወደተግባር መግባት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

የልዑካን ቡድኑ በቀጣይ ቀናት የቡልቡላ እና የይርጋለም አግሮ -ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.