Fana: At a Speed of Life!

ኃላፊነታቸውን በማይወጡ አመራሮች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የሐረሪ ክልል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 23፣2014 (ኤፍ ቢሲ) አመራሩ ሁሉንም ህዝብ በእኩልነት በማገልገል ሃላፊነቱን መወጣት ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡

ርዕሰ-መስተዳድሩ ÷ ሃላፊነታቸውን በማይወጡና ህዝብ እንዲማረር በሚያደርጉ በየደረጃው በሚገኙ አመራሮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ነው ያመላከቱት፡፡

በክልሉ እየተሰሩ ያሉ የልማት ሥራዎች በተለይም የገጠሩን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

በክልሉ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ በማኅበር ለተደራጁ አካላት መሬት የመስጠት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመው ተጠክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት።

ከፕሮጀክቶች መጓተት ጋር ተያይዞም ከግንባታ እቃዎች ዋጋ መናር ተፅእኖ ቢያሳድርም በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚታዩ የሌብነት ችግሮች መከላከል እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡

የትምህርትና ጤና አገልግሎት ጥራትን ለማጎልበትም የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፈተሽ በንቅናቄ መልክ ይሰራልም ተብሏል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ÷ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሥራዎችን በማከናወን የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ከገጠር የመሠረተ ልማት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በተለይ ማህበረሰቡን የመብራት ችግር ለመቅረፍ አስፈላጊውን በጀት ተመድቦ በገጠር በሚገኙ ቀበሌዎች የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከዚህ ባሻገር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የደላሎች ሰንሰለት በመበጣጠስ አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ ለተጠቃሚው የማድረስ ስራም በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል፡፡

ለአርሶ አደሮች ምርት መሸጫነት እየተከናወነ የሚገኘው ፕሮጀክት መጓተትን በሚመለከትም ያሉ ችግሮች ተፈትሸው ፕሮጀክቱ እንዲጠናቀቅና አገልግሎት እንዲሰጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በህገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ላይ በሚሳተፉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ስራም በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ነው ያመላከቱት፡፡

የሐረሪ ክልል ምክር ቤት እያካሄደው በሚገኘው 6ኛ ዙር 1ኛ አመት 2 መደበኛ ጉባኤ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪና ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ምላሽ መስጠታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.