Fana: At a Speed of Life!

በጸጥታ እና በሃይል አቅርቦት ችግር ስራ ያቋረጡ 2 ሺህ የሚጠጉ ኢንተርፕራይዞችን ስራ ለማስጀመር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት፣ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት በጸጥታ እና በሃይል አቅርቦት ችግር ስራ ያቋረጡ 1 ሺህ 929 ኢንተርፕራይዞችን ስራ ለማስጀመር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ያለፉት ዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም የተቋሙ አመራሮች፣ ሰራተኞች፣ የገንዘብ ሚኒስቴር አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተገምግሟል።

የኢንተርፕራይዙ ዳይሬክተር አቶ ብሩ ወልዴ፥ ባለፋት ዘጠኝ ወራት 2 ሺህ 907 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ተቋቁመው ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ አዲስ ኢንተርፕራይዞችም 36 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ነው የገለጹት።

ነባር ኢንተርፕራይዞችን ከማጠናከር አንጻርም 7 ሺህ 613 በላይ ነባር ኢንተርፕራይዞችን በማጠናከር ለ37 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠር መቻሉ የተመላከተ ሲሆን ÷በአንጻሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ሺህ 929 በላይ ኢንተርፕራይዞች በጸጥታ ችግር፣ በሃይል አቅርቦት እና በግብዓት እጥረት ስራ ማቋረጣቸውን አንስተዋል።

ስራ ካቋረጡት ኢንተርፕራይዞች ውስጥ አብዛኞቹ አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ ሙሉ በሙሉ የወደሙ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

እነዚህን ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ ለማስገባትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በቀጣይ የአምራች ኢንተርፕራይዞችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የዘርፉን ተግዳሮቶች እና ማነቆዎች መፍታት እንደሚገባ ነው የተጠቆመው።

በዘርፉ የሚታዩ የመሠረተ ልማት ችግር፣ የመብራት መቆራረጥ፣ የብድር አቅርቦት ውስንነት፣ የማምረቻና መሸጫ ሼዶች አቅርቦት እና ሌሎች ማነቆዎችን በተቀናጀ መልኩ ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ተገልጿል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማሳለጥ ፣ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ገቢ ምርቶችን በመተካት የገበያ አቅርቦት ጉድለት በመቅረፍ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋኦ እንዲሚያበረክት ታውቆ በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል ፡፡

በመላኩ ገድፍ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.