በውድ ዋጋ የተገዙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ንብረቶች ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው ለብክነት መዳረጋቸውን የፌዴራል ኦዲተር ቢሮ ገለጸ
አዲስ አበባ፣መጋቢት 23፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአራት ማዕከላት በውድ ዋጋ የተገዙ ንብረቶች ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው ለብክነት መዳረጋቸውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ቢሮ ገልጿል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የንብረት አስተዳደር የኦዲት ሪፖርት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው 2012/13 በጀት ዓመት የንብረት አስተዳደር አፈጻጸምና ውጤታማነት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።
በውይይት ወቅት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ እንደገለጹት÷ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአራት ማዕከላት ላይ በተደረገ ኦዲት በርካታ ጉድለቶች ታይቷል።
ኦዲቱ ከ2010 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የሎጂስቲክስ፣ ንብረትና ፋሲሊቲ ዳይሬክቶሬት ዴስክ ላይ በምጣኔ ኃብታዊ፣ በቀልጣፋነትና ውጤታማነት በአራት ማዕከላት ላይ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አገልግሎቱ በ2006 ዓ.ም ንብረቶችን የሚያስተዳድርበት ፖሊሲና መመሪያ ቢያወጣም በናሙና በታዩት በጎፋ ማዕከላዊ ዕቃ ግምጃ ቤት፣ በኮተቤ የተሸከርካሪ ጥገናና የትራንስፖርት አስተዳደር፣ በምዕራብና በደቡብ አዲስ አበባ ዲስትሪክቶች የዕቃ ግምጃ ቤቶች ላይ መመሪያው አልተተገበረም ነው ያሉት።
በአገልግሎቱ የኦዲት ቡድኑ በጎፋ የማዕከላዊ ዕቃ ግምጃ ቤት ከያዙት ግዙፍ፣ ብዛት ያላቸውና ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው ንብረቶችን ባገናዘበ መልኩ የሰው ኃይል በአግባቡ ባለመደራጀቱ የንብረት ብክነት አጋጥሟል ብለዋል።
በአራቱም የዕቃ ግምጃ ቤቶች ድንገተኛ ቆጠራ የማይካሄድ በመሆኑ በበርካታ ሚሊየኖች የሚገመት ዋጋ ያላቸው ንብረቶች እና ለብክነትና እና ለስርቆት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም በጎፋ ማዕከላዊ ዕቃ ግምጃ ቤት ከ7 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተገዙ ብዛታቸው 8 ሺህ 601 የሆኑ ዕቃዎች ከ15 ዓመት በላይ በመጋዘን ቁጥር ሁለት ውስጥ ታሽጎ እንደሚገኝ በኦዲት ግኝቱ ተረጋግጧል።
በተመሳሳይ የተሽከርካሪ ጥገናና ትራንስፖርት አስተዳደር በመጋዘን 13 ከ10 ዓመት በላይ አገልግሎት ሳይሰጡ 3 ሺህ 595 የተሽከርካሪ ዕቃዎች በኦዲት ግኝቱ ተረጋግጧል።
በተቃራኒው 35 ሚሊዮን ብር በላይ ለተሽከርካሪ ኪራይ መከፈሉን ጠቁመው፤ በሥራ ላይ ያሉትም ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ጠቋሚ ጌጅ በትክክል እንደማይሰራ ገልጸዋል።
በደቡብና በምዕራብ አዲስ አበባ ዲስትሪክቶች በከፍተኛ ዋጋ የተገዙ ትላልቅ ንብረቶች እየተዘረፉ መሆኑን በኦዲት ግኝት ለማወቅ ተችሏል ብለዋል።
ቋሚና አላቂ ንብረቶችን ከብልሽትና ከምዝበራ ለመከላከል በተሟላ ሁኔታ ቁጥጥርና ክትትል ባለመኖሩ ንብረት እየባከነ ይገኛል ሲሉም ጠቁመዋል።
በጎፋ ማዕከላዊ ዕቃ ግምጃ ቤት ከ5 ሺህ በላይ ዕቃዎች ለረዥም ጊዜ የተቀመጡና ከዚህም ውስጥ ከ651 ብቻ ሲታዩ ከ59 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን በኦዲት ተገኝቷል ብለዋል።
ከተቋሙ ሁለት ተሽከርካሪዎች አንድ V8 እና አንድ ሌላ ተሽከርካሪ መጥፋታቸውን በኦዲት ግኝቱ መታወቁንም ጠቅሰው፤ የንብረት አቀማመጥ፣ የቆይታ ጊዜና ለብልሽት የተጋለጠና ለመቆጣጠረ የሚያስቸግር አሰራር በተቋሙ ውስጥ መኖሩንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።