Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የኀብረተሰቡን ኑሮ የሚለውጡ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው -ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣የካቲት 18፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የኀብረተሰቡን ኑሮ የሚለውጡ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

በርዕሰ መስተዳድሩ የተመራ የልዑካን ቡድን ምዕራብ ሸዋ ዞን ጊንጪ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘውን የ’ኬኛ ቢቬሬጅ ኢንዱስትሪ’ እና የአምቦ-ጉደር አስፋልት መንገድ ግንባታን ጎብኝቷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት፥ በክልሉ ከሶስት ዓመት ወዲህ የኀብረተሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እየገቡ ነው ብለዋል።

በዚህም በማዕድን፣ በሞተር መገጣጠሚያ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚሰሩ 16 ኩባንያዎች ተቋቁመው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ከእነዚህ መካከል በ’ኬኛ ቢቬሬጅ ኢንዱስትሪ’ ስር የሚገነባው ‘የኬኛ ቢራ ፋብሪካ’ በተሻለ የግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ ፋብሪካውን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት ለማስገባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኬኛ ቢቨሬጅ ኢንዱስትሪ ስራ አስኪያጅ አምሳል መገርሳ በበኩላቸው የፋብሪካው ግንባታ በተቀመጠለት እቅድ መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዚህም በታቀደው የጊዜ ሰሌዳ ወደ ምርት እንደሚገባ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በክልሉ ርእሰ መስተዳድር የሚመራው ልዑክ ጉብኝት ያደረገበት ከአምቦ-ጉደር የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታም በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑ መገለፁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሁለቱን ከተሞች በኢኮኖሚና በማህብራዊ ኑሮ ለማገናኘት ታስቦ እየተገነባ ያለና 19 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ እየተገነባ ሲሆን÷ ግንባታውን የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እያከናወነ ይገኛል፡፡

የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አስመራ አቤቤ የግንባታው አፈጻጸም 20 በመቶ መድረሱን ተናግረው ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ቢያዝለትም ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ የግንባታ ሂደቱ መጓተቱን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.