በትግራይ ክልል 1ሺህ 601 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ መለቀቃቸው ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል 1ሺህ 601 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ መለቀቃቸውን የክልሉ ጸጥታ ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ተኪኡ ምትኩ ትላንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፥ ለኮረናቫይረስ ተጋላጭ የሆኑ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲለቀቁ የክልሉ መንግስት ወስኗል።
የተለቀቁት ታራሚዎች አንድ ሶስተኛውን የማረሚያ ቤት ቆይታቸውን ያጠናቀቁ፣ መልካም ስነምግባር ያሳዩና ለይቅርታው ብቁ በመሆናቸው የተለዩ እንደሆኑም ተናግረዋል።
ታራሚዎቹ ከዛሬ ጀምሮ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ትራንስፖርት በልዩ ሁኔታ እንደተዘጋጀላቸው መግለፃቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።
በተመሳሳይ ዜና በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመቆጣጠርና ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ለ81 ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል።
የክልሉ ፕሬስ ሴክረታሪያት ጽህፈት ቤት እንደገለፀው፥ ይቅርታ የተደረገላቸው በቀላል ወንጀል እስከ ሶስት ዓመት ተፈርዶባቸው ያሉና በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በአመክሮ እስከ አንድ ዓመት የቀራቸው ናቸው።
የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ አኳይ ኡቡቲ እንዳሉት የይቅርታ መስፈርቱን የሚያሟሉ በቀላል ወንጀል እስከ ሶስት ዓመት የተፈረደባቸውና በአግባቡ የታረሙ ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ ከ3ቱ ማረሚያ ቤቶች 81 የሚደርሱ ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጎላቸዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ በይቅርታ ከተፈቱት 81 ታራሚዎች በተጨማሪ በጊዜ ቀጠሮ ማረሚያ ቤት ያሉ 88 ግለሰቦች በዋስ እንዲለቀቁ መደረጉንም አብራርተዋል።