Fana: At a Speed of Life!

በስዊዘርላንድ በአማራና አፋር ክልሎች ጉዳት ለደረሰባቸው ተቋማት የሚሆን ሃብት የማሰባሰብ ዘመቻ ተጀመረ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በስዊዘርላንድ የሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በአማራና በአፋር ክልሎች ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት የሚያስችል የሃብት ማሰባሰብ ዘመቻ በይፋ ጀምረዋል::

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉት በስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዘነበ ከበደ÷ በአገሪቱ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በአገራችን በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳት እስከዛሬ እያደረጉት ላለው አጠቃላይ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ሪስቶር ሆፕ እና ገበታ ለወገኔ በተሰኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የተጀመረው የሃብት ማሰባሰብ ስራም እጅግ የሚያበረታታ መሆኑን የገለፁት አምባሳደሩ÷ የሃብት ማሰባሰቡ ስራ የተያዘለትን ግብ እንዲመታም ኤምባሲው አስፈላጊውን ድጋፍ  እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

በበይነ መረብ  የተሳተፉት  የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ማርታ ምንውየለት በበኩላቸው÷በሁለቱ ክልሎች ጤና ተቋማት ላይ በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት በመንግስት እንዲሁም በአጋር አካላት እየተደረገ ስላለው የማደራጀት ስራ እና ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ሁለቱ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን ለመደገፍ እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ ያደነቁት ክፍተኛ አማካሪዋ÷ የተሰበሰበው ሃብት ወደ አገር ቤት ደርሶ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚደርግ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ በነበረው የበይነ መረብ ውይይትም ከተሳታፊዎች ከ7 ሺህ በላይ የስዊዝ ፍራንክ  የተሰበሰበ ሲሆን÷ በቀጣይም ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መገለጹን  ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል::

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.