መንግስት የገበያ ስርዓቱን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንደሚያደርግ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ተናገሩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ገበያ ስርዓቱን እንደ ቴሌኮም ዘርፍ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንደሚያደርግ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ተናገሩ፡፡
በየዕለቱ ከቁጥጥር እየወጣ ያለው የዋጋ ንረት የኢኮኖሚ ዕድገቱን ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል ተብሏል፡፡
ለዚህም መንግስት የጥቅል ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲፈጥር በማድረግ የዜጎችን ገቢ ማሳደግ የሚችልባቸውን አማራጮች ማሰብ ይኖርበታል፤ እስከዛው ግን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ምክንያቱን በለየ መልኩ መፍትሄ እንዲመጣ ከመንግስት ይጠብቃል፡፡
እንደ ገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ገለፃ፥ በዓለም ገበያ የምርቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው፤ አሁን ላይ ላለው የዋጋ ንረት ቀዳሚው ምክንያትም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ዋጋ በቀጥታ ሸማቹ ላይ እንዲያርፍ መደረጉ ነው፡፡
የአንዳንድ ምርቶች ዋጋ ማለትም በብረት፣ ዘይት፣ ነዳጅና የመሳሰሉት ከውጭ የምናስገባቸው ምርቶች ዋጋቸው እስከ እጥፍ መጨመር በሀገር ቤት ያለው የጸጥታ ሁኔታም በምርት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል የፈጠረና በዋጋ ንረቱ ላይ ትልቅ አበርክቶ አለው ነው ያሉት፡፡
ሌላው መንግስት ወጪውን እየሸፈነበት ያለው የገንዘብ ፖሊሲም በራሱ ጫና የሚፈጥር ነው፤ እነዚህን በጊዜ ሂደት እያስተካከልን መሄድ ካልቻልንም የባሰ ሊመጣ ይችላል ብለዋል፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች የራሳቸውን ጊዜ ጠብቀው እንደሚስተካከሉ ይጠበቃል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የጸጥታ ሁኔታው መንግስት ሰላምን በመምረጡ በተሻለ ደረጃ ምርቶች እንዲቀርቡ ዕድል እንደሚፈጥር ይታሰባል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ግን የሀገሪቱ የገበያ ስርዓት በጥቂቶች ብቻ ያለ በመሆኑ መንግስትን የፈጠነ ማሻሻያ እንዲያስብ እንዳደረገው ተጠቁሟል፡፡
ለዚህም የገበያ ስርዓቱ ለውድድር ክፍት መሆን አለበት ያሉት ዶክተር ዕዮብ ዘርፉ ለውድድር ክፍት ሲሆን፥ 200 በመቶ ካላተረፈ ያላተረፈ የሚመስለው ነጋዴ ወደ ቀልቡ እንዲሰበሰብ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የቴሌኮም ኢንዱስትሪው ለውድድር እንደተከፈተ ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ በቅርቡ ደግሞ የሀገሪቱ የግብይት ስርዓት ለዓለም አቀፍ የንግድ ኩባንያዎች ክፍት እንደሚደረግ ነው ያስታወቁት።
ከእነዚህ ምክንያቶች ባለፈ ግን በዶላርና ብር መሃል ያለው የምንዛሬ ተመን በየጊዜው እንዲሰፋ መደረጉ ለዋጋ ንረቱ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ተገልጿል፡፡
“የውጭ ምንዛሬ ላይ የጀመርነው ማሻሻያ የጎንዮሽ ጉዳት የለውም የሚል የመንግስት አካል የለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ነገር ግን ሊያመጣ የሚችለውን ተጽዕኖ ተቋቁሞ የሚገኘውን ጥቅም ማሳካት ያስፈልጋል፤ ማሻሻያው መዘግየቱ በራሱ የፈጠረው ተጽዕኖ አለ፤ ያን በፍጥነት ተግብረን ችግሮችን ለመቅረፍ እንሰራለን” ነው ያሉት።
ማሻሻያው በተለይም በወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስገኝቷል ቢባልም ችግሮች በተደራረቡ ጊዜ ግን አንዳንድ ማሻሻያዎችን ማዘግየት እንደ መፍትሄ ይቆጠራልም ነው ያሉት፡፡
በባሃሩ ይድነቃቸው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!