Fana: At a Speed of Life!

የተዛባውን ማክሮ ኢኮኖሚ ለማስተካከል የሶስት ዓመት እቅድ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተዛባውን የሀገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ለማስተካከል የሶስት ዓመት እቅድ መዘጋጀቱን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ከፍተኛ የሆነ የስራ አጥ ቁጥር፣ ከቁጥጥር ውጪ እየወጣ ያለ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት፣ የበዛ የመንግስት ወጪ የሚታይበት በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ያለችበት የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት አሁንም እንዳለ ነው።

ሀገሪቱ የቆየችበት ጦርነት ደግሞ ለዚህ ትልቁን አስተዋጽዖ አበርክቷል ነው የሚሉት።

ከዚህ ቀደም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቱ ምንጭ ሀገሪቷ አይኗን ጨፍና የተበደረቻቸው ውድ ብድሮች ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተው ሀገሪቱን የከፋ ሁኔታ ውስጥ መክተቱ ነበር ያሉት ሚኒስትሯ፥ አሁን ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት የገጠመው የበጀት እጥረት የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባት ምንጭ ሆኗል ነው የሚሉት።

ይህን በበጀት በኩል የሚመጣ መዛባትን ለመከላከል ፕሮጀክትን በሚገባ ማስተዳደር እና ወጪን መቆጠብ በቀጣይ ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎች መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢኮኖሚው መሻገር ያልቻላቸው በርካታ ችግሮች እንዳሉበት በማንሳት ይህን ለማስተካከል ደግሞ የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባ ዝርዝር እቅድ በማስፈለጉ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ የተቀዳ እና አሁናዊነትን የተጎናጸፈ የሶስት ዓመት እቅድ ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት መተግበር የሚጀምረው እቅዱ ጥራት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማስመዝገብ የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ዋነኛ ምሰሶው ያደረገ ነው።

በቀጣይ ዓመት የሚቀርበው የመንግስት በጀትም ዋነኛ ትኩረቱ ወጪን በቆጠበ መልኩ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቱን ማከም የሚያስችል እንዲሆን ሆኖ እንደሚዘጋጅ ዶክተር ፍፁም ጠቁመዋል።

ሌላው እቅዱ ዓለም አቀፍ ሁኔታን ከግምት ያስገባም ነው። የ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ሲዘጋጅ ሩሲያና ዩክሬን የገቡበት ግጭት ሊታሰብ አይችልም የሚሉት ሚኒስትሯ፥ ይህን ተከትሎ የሶስት ዓመቱ እቅድ ሀገር ቤት የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ታሳቢ አድርጓል ነው ያሉት፤ ለአብነትም የአፈር ማዳበሪያ የሚሸመትባቸው ሀገራት የምርት ጥሬ እቃ ምንጮቻቸው ሩሲያና ዩክሬን መሆናቸው በማንሳት።

ከሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ደግሞ ድርቅን የሚቋቋም ኢኮኖሚን መገንባት በተለይም ለውሃ ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ድርቅ ሲመጣ አብረው የሚደርቁ የውሃ ጉድጓዶች የማይኖሩበትን አቅም መፍጠርን ታሳቢ አድርጓል።

ጦርነቱ የፈጠረው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት መቀጠሉ አይቀርም ያሉት ዶክተር ፍፁም፥ እውነተኛ ተጽዕኖውም በቀጣይ ዓመታት በደንብ እንደሚታይ ይጠበቃል ነው ያሉት።

ይህን ተከትሎም እቅዱ ጦርነቱ ያስከተላቸውን ጉዳቶች ለማስተካከል ያለመ ነው ብለዋል፤ ደራሽ እህልን አጠናክሮ ማስቀጠልና ማህበራዊ ተቋማትን አብልጦ በመገንባት ውጤታማ መሆን እንደታሰበ በመጠቆም።

በጦርነቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በብዙ ተጎድቷል። ጉዳቱን ለማካካስ መንግስት በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ጽህፈት ቤት እንዳቋቋመና ጽህፈት ቤቱ የሚታይ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው እንደታመነበት ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የመልሶ ማቋቋሙና መገንባቱ እቅድ የትግራይ ክልልንም ታሳቢ ማድረጉን የጠቆሙት ዶክተር ፍፁም፥ እቅዱ ጦርነቱ ከመከሰቱ በፊት ትልቅ ግምት የተሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለማነቃቃት ታስቧልም ነው ያሉት።

ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ አምራች ኢንዱስትሪው እና የአገልግሎት ዘርፉ ጦርነቱ ባይከሰት ያሳካሉ ተብሎ የሚጠበቀው ውጤት ከፍተኛ ቢሆንም ሳይሳካ መቅረቱን በመግለፅ፥ በሶስት ዓመት ግን ያንን ውጤት ማካካስ የሚያስችል እቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

 

 

በባሃሩ ይድነቃቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.